የሀገር ውስጥ ዜና

ሀብት ከሚባክንበትና ኪሣራ ከሚመዘገብበት ታሪክ መውጣት ተችሏል – ም/ጠ/ሚ ተመስገን ጥሩነህ

By Feven Bishaw

November 12, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በተቋም ግንባታ ማዕቀፍ በተሠራዉ ሪፎርም በርካታ የሀገር ሀብት ከሚባክንበትና በየዓመቱ ኪሣራ ከሚመዘገብበት ታሪክ መውጣት መቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ የሆኑ አስፈጻሚ አካላት የ2017 በጀት ዓመት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸም ግምገማ ዛሬ መጀመሩን አስመልክቶ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልዕክት÷ የተቋማት ግንባታ ሥራችን የሀገረ መንግሥት ግንባታዉ ዋና ምሦሦ ነው ብለዋል።

በተቋም ግንባታ ማዕቀፍ በተሠራዉ ሪፎርም በርካታ የሀገር ሀብት ከሚባክንበትና በየዓመቱ ኪሣራ ከሚመዘገብበት ታሪክ መዉጣት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የሀገርን ኢኮኖሚ የሚደግፉ እና በቢሊየኖች የሚቆጠር ብር በየዓመቱ ትርፍ የሚያስመዝግቡ፣ ለበርካቶች የሥራ ዕድል የሚፈጥሩ፣ ለዕዉቀት እና ለቴክኖሎጂ ሽግግር አስተዋጽዖ የሚያበረክቱ ተቋማት መፈጠራቸውን ገልፀዋል፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ተጠሪ በሆኑ ሁሉም ተቋማት የተጀመረዉ ሪፎርም ባለፉት ዓመታት የሚለካና የሚቆጠር ውጤት ማምጣቱንም አመላክተዋል፡፡

በዛሬዉ መድረክ በዋናነት በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ ሩብ ለማሳካት ከታቀዱ ጉዳዮች ውስጥ ዋና ዋና አፈጻጸሞች እንደሚገመገሙም ጠቁመዋል፡፡

በዚህም በተገቢው መንገድ ያሳካናቸዉን በማየት በጉድለት የታዩትንም በመንቀስ፣ ትኩረት የሚፈልጉ ጉዳዮችን በመለየት፣ የጋራ ርብርብ ለማድረግ በቀጣይ ለሚኖረን ምዕራፍ የተሻለ መነሳሳት የምንፈጥርበት መድረክ ይሆናል ብለዋል።