አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ የ2024 ተስፋ ከሚጣልባቸው ሦስት ሴት አትሌቶች ውስጥ ተካትታለች፡፡
በዘንድሮ የዓለም አትሌቲክስ ምርጥ ከ20 ዓመት በታች ወይንም ተስፋ የሚጣልባቸው አትሌቶችን የዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን አስተዋውቋል፡፡
በዚህም አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ በሴቶች የ2024 ተስፈኛ ኮከብ አትሌት ሽልማት የመጨረሻ ሦስት እጩዎች ውስጥ ተካትታለች።
እጩዎቹ ስፖርቱ በዚህ ዓመት በተለያዩ የውድድር መድረኮች ድንቅ ብቃት ያሳዩ መሆኑ ተገልጿል።
በዚህም በፓሪስ 2024 ኦሊምፒክ ጨዋታዎች፣ በዓለም አትሌቲክስ የቤት ውስጥ ሻምፒዮና፣ በዓለም አትሌቲክስ ከ20 ዓመት በታች ሻምፒዮና፣ የዓለም አትሌቲክስ ሀገር አቋራጭ ሻምፒዮና እና ሌሎችም ላይ የታዩ አትሌቶች ናቸው ተብሏል።
የ2024 የሴቶች ‘ራይዚንግ ስታር’ ሽልማት አሸናፊ በዓለም አትሌቲክስ መድረኮች በፈረንጆቹ ታህሳስ 1 እንደሚገለጽ ከዓለም አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የ19 ዓመቷ አትሌት ሲምቦ ዓለማየሁ፥ በ3 ሺህ ሜትር መሰናክል በፔሩ ሊማ የዓለም ከ20 ዓመት በታች ስታሸንፍ በፓሪስ ኦሊምፒክ ደግሞ 5ኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቃለች።
በ2024 ከሲምቦ ዓለማየሁ በተጨማሪ አንጄሊና ቶፒች ከሰርቢያ በከፍታ ዝላይ እንዲሁም ያን ዚዪ ከቻይና በጦር ውርወራ ተስፋ የሚጣልባቸው እጩ ሴት አትሌቶች ውስጥ ተካትተዋል፡፡
አትሌት ሰለሞን ባረጋ በፈረንጆቹ 2019 ይህን ሽልማት በማሸነፍ ብቸኛው ኢትዮጵያዊ መሆኑ ይታወቃል።