አዲስ አበባ፣ ሕዳር 3፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) 19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በሀገር አቀፍ፣ በክልሎችና በሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ባሳተፈ መንገድ እንደሚከበር ተገለጸ።
የፌደሬሽን ምክር ቤት በዓሉን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፥ የበዓሉ ሀገር አቀፍ ማጠቃለያ መርሐ-ግብር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ ለተከታታይ አምስት ቀናት እንደሚከበር አስታውቋል።
በዚህም ሕዳር 25 የወንድማማችነት ቀን፣ ሕዳር 26 የአብሮነት ቀን፣ ሕዳር 27 የደቡብ ኢትዮጵያ ቀን፣ ሕዳር 28 የምክክር ቀን እንዲሁም ሕዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም የኢትዮጵያውያን ቀን በሚል ስያሜ በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ተገልጿል።
በብዝኃነት ላይ የተመሰረተ አንድነት ስር እንዲሰድና እንዲዳብር በማድረግ ህብረብሔራዊ አንድነትን ማጎልበት የበዓሉ ዋና ዓላማ መሆኑን መግለጫውን የሰጡት የበዓሉ ዋና አስተባባሪ ወ/ሮ ባንችይርጋ መለሰ ተናግረዋል።
19ኛው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል “ሀገራዊ መግባባት ለህብረብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሀሳብ ይከበራል።
በዙፋን ካሳሁን እና ወንድሙ አዱኛ