የሀገር ውስጥ ዜና

የአዲስ አበባ ከተማ ካቢኔ 2ኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ያለበትን ደረጃ ገመገመ

By Mikias Ayele

November 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ በ4ኛ ዓመት 3ኛ መደበኛ ስብሰባው ሁለተኛ ዙር የኮሪደር ልማት ሥራ ያለበትን ደረጃ በጥልቀት ገምግሟል፡፡

በመድረኩ የልማት ተነሺዎች የተስተናገዱበት አግባብ፣ በመንግስት የሚኖሩ የነበሩ የተነሱበት አግባብ እና መሰረተ ልማት የተሟሉላቸው መሆኑ ተገምግሟል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የግል ተነሺዎች ደግሞ የካሳ የ3 ዓመት የቤት ኪራይና ምትክ መሬት መውሰዳቸውን፣ የትራንስፖርት አቅርቦት እና የሞራል ካሳ በሕጉ መሰረት የተከፈለ መሆኑ የተተነተነ ሪፖርት በየኮሪደሩ አስተባባሪዎች ቀርቦ መገምገሙ ተመላክቷል፡፡

ሁሉም ሕጋዊ ውል ወይም ሰነድ ኑሯቸው እንዲሁም በመጠለያ በተገኙበት ተጠልለው የሚኖሩ ነዋሪዎችን ሁሉ የቤት መስተንግዶ እና የቤት መሰረተ ልማቶች በተሟላላቸው እጅግ የተሻለ ንፁህና መሠረታዊ መገልገያዎች የተሟሉላቸው ቤቶች የተስተናገድ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

ለመኖር ምቹ አካባቢ ያገኙ ስለመሆኑ እና አንዳንድ ሳይቶች ላይ የመንገድ ደረጃውን ለማሻሻል ግንባታ እየተካሄደ ስለመሆኑ ሪፖርት ቀርቦ ካቢኔው በፍጥነት እንዲጠናቀቅ ውሳኔ አስተላልፏል።

ሌሎች ሳይቶች ላይ አስፈላጊው መሰረተ ልማት ተጠናቅቆ ነዋሪዎች የየዕለት ኑሯቸውን እንዲቀጥሉ መደረጉም ነው የተገለጸው፡፡

የማህበራዊ ኑሯቸው ሳይበታተን እድር ፣ ማህበር እና አብሮነታቸው የመሰረቱት ማህበራዊ መስተጋብር እንደተጠበቀ መስተናገዳቸውም ተጠቅሷል፡፡

አቃቂ ፣ገላን ጉራ ፣ፉሪ ሃና ፣አራብሳ አምስት እና ስድስት አያት ሶስት፣ ላፍቶ ሃይሌ ጋርመንት እና ለሚኩራ አጠገብ የተሰሩት ሎኮስት ፣አየርጤና ቂርቆስ ለገሃር አካባቢ ፣አራዳ ሰባ ደረጃ አካባቢ በመሃል ከተማ የተገነቡ ቤቶች ላይም መስተናገዳቸውንና እና አፈፃፀሙም ጥሩ መሆኑን ካቢኔው ገምግሟል።

የመሠረተ ልማት ቅንጅት አካላት ከከተማ እስከ ፌዴራል ተቋማት የነበራቸው ተሳትፎ በምሳሌነት የሚጠቀስ መሆኑን ካቢኔው በጥንካሬ አንስቷል፡፡

በተጨማሪም መሬት እና ካሳ ምትክ እስካሁን ድረስ ብቻ ከ4 ነጥብ 6 ቢሊየን ብር በላይ መከፈሉን የሁለት ዓመት የቤት ኪራይ መከፈሉን እና ቀሪ ተነሽዎችም ቅድመ ዝግጅት ሂደት ካቢኔው በጥንካሬ ገምግሟል ።

በሌላ በኩል በኮሙኒኬሽን ሥራዎችን በደንብ ደጋግሞ ለሕዝብ መረጃን ማድረስ ላይ ከዚህ በላይ ማድረስ እና ተደጋጋሚ የሚዲያ ሽፋን ያላቸው የመረጃ ስርጭት ለህብረተሰቡ መድረስ እንዳለበት ካቢኔው አሳስቧል።

መረጃን የሚያዛቡ እና ሀገር እንዳትለማ ውዥንብር በሚፈጥሩ የተለያዩ ዝንባሌዎች የሚያሳዩ የመረጃ ምንጮችን እና አካላት ላይ ሕጋዊ ርምጃ በመወሰድ እንዳለበት በአፅንኦት አንስተዋል ፡፡

በ2ኛው ዙር ኮሪደር ልማት ስራ 2 ሺህ 879 ሄክታር ስፋት፣ 135ኪሎ ሜትር የኮሪደር ርዝመት ያለው ሲሆን÷ 240 ኪሎ ሜትር የአስፋልት መንገድ፣ 237 የእግረኛ መንገድ ፣ 32 የህፃናት መጫዎች ቦታዎችና 79 የህዝብ መዝናኛ ቦታዎች እንደሚያካትት ተገልጿል፡፡

በተጨማሪም 114 የታክሲ እና አውቶቡስ መጫኛ እና ማውረጃ፣ 58 የኤሌክትሪክ መኪና ቻርጅ ማድረጊያ ቦታዎች፣ 368 ሄክታር አረንጓዴ ልማት ሽፋን ያላቸው ቦታዎች፣ የ 111 ኪሎ ሜትር ሳይክል መንገድ ፣ 17 የስፖርት ማዘውተሪያ ቦታዎች፣ 106 የህዝብ መረዳጃ ቤቶች፣ 121 ኪ.ሜ የፍሳሽ ማስወገጃ መስመር ፣ 182 ኪ.ሜ ድሬኔጅ መውረጃ መስመር ፣ 50 የተሸርካሪና እግረኛ መተላለፊያ እና 75 ኪ .ሜ ሪቴይኒንግ (የድጋፍ ግንብ) ስራዎችን የሚያካትት መሆኑ ተመላክቷል፡፡

ይህንኑ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ክትትል ማሳደግ፣ ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ የተተገበሩ የአንደኛ ዙር ኮርድር ልማት ልምዶች ተቀምረው ለ2ኛው ዙር በተሻለ ብቃት መስራት እንደሚያስፈልግና ቅንጅታዊ አሰራርንም በተጠናከረ መልኩት አሳድጎ በጥንካሬ አሁን ካለው በላይ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ካቢኔው ማሳሰቡን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመልክቷል፡፡