የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና አውስትራሊያ ትብብራቸውን ለማጠናከር እንደሚሰሩ ገለጹ

By Mikias Ayele

November 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴዔታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ በኢትዮጵያ የአውስትራሊያ አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት ጋር ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ ÷ ሀገራቱ የሁለትዮሽ ግንኙነታቸውን ማጠናከርና በንግድና ኢንቨስትመንት ያላቸውን ትብብር ማስፋት እንደሚገባቸው ገልጸው ÷ለዚህም ኢትዮጵያ ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል፡፡

የሁለቱን ሀገራት የጋራ ተጠቃሚነት ባማከለ መልኩ ኢኮኖሚ እና አቪዬሽንን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ መስኮች ትብብራቸውን ለማሳለጥ ትኩረት አድርገው መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

አምባሳደር ጁሊያ ኒብሌት በበኩላቸው ÷ሁለቱ ሀገራት በግብርና፣ በሰብዓዊ ድጋፍ፣ በምግብ ዋስትና፣ በትምህርት እና በስርዓተ ጾታ እኩልነት ላይ ያስመዘገቧቸውን የትብብር ስኬቶች አድንቀዋል።

የተገኙ ውጤቶችን በማስቀጠል ሁለቱ ሀገራት በተለያዩ መስኮች ያላቸውን የሁለትዮሽ ትብብር አድማስ ማስፋት እንደሚገባም አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እና አውስትራሊያ የሁለትዮሽ አጋርነታቸውንና በባለብዝሃ ወገን መድረኮች ያላቸውን ትብብር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሚሰሩ መገለጹንም የሚኒስቴሩ መረጃ ያመለክታል።