Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሳንባ ምች በምን ምክንያት ይከሰታል?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሳንባ ምች(ኒሞኒያ) አብዛኛውን ጊዜ በኢንፌክሽን ምክንያት የሚመጣ የሳንባ መቆጣት ነው።

የበሽታው ምክንያት ከቀላል እስከ ከባድ የሚደርስ የሳንባ ኢንፌክሽን ሲሆን÷ ኢንፌክሽኖች በሳንባዎች ውስጥ የሚገኙትን የአየር ከረጢቶች በፈሳሽ ወይም በመግል ሲሞሉ ለመተንፈስ እና ኦክስጅንን ወደ ደም ውስጥ ለማስገባት አስቸጋሪ ያደርገዋል።

እድሜያቸው ከ2 ዓመት በታች የሆኑ ህጻናት እና ከ65 ዓመት በላይ የሆኑ አዛውንቶች በተዳከመ የበሽታ መቋቋም ስርዓት ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ለሳንባ ምች ተጋላጭ እንደሆኑ በዘርፉ የተጠኑ ጥናቶች አመላክተዋል፡፡

በተጨማሪም እንደ የልብ ህመም፣ የስኳር በሽታ፣ የሳንባ በሽታ፣ በሽታ የመከላከል አቅምን የሚያዳክሙ እና አንዳንድ ካንሰሮችን የመሳሰሉ ሥር የሰደዱ የጤና እክሎች ያለባቸው ሰዎች የበለጠ ተጋላጭ ናቸው።

የሳንባ ምች በሳል እና በማስነጠስ ወቅት በሚኖሩ የፈሳሽ ጠብታዎች፣ ወይም እቃዎችን በመንካት እና ጀርሞችን ወደ ሰውነት በማስገባትና በሌሎች ምክንያቶች ሊሰራጭ ይችላል።

በሽታው በአብዛኛው ከሚያሳያቸው ምልክቶች መካከል ከፍተኛ የሆነ ሳል፣ትኩሳት እና ላብ፣የድካም ስሜት፣የምግብ ፍላጎት መቀነስ፣ራስ ምታት፣ ለመተንፈስ መቸገርና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ ፡፡

የሳንባ ምች ከተከሰተበት ሁኔታ በመነሳት ሆስፒታል ለረጅም ጊዜ በመቆየት ምክንያት የሚከሰት የሳንባ ምች፣የሞቀ ሰውነት ከቅዝቃዜ ጋር ሲጋጭ የሚከሰት የሳንባ ምች፣ንጽህናውን ያልጠበቀ ምግብና መጠጥ በመውሰድና አልኮል አብዝቶ በመውሰድ የሚመጣ የሳንባ ምች ፣ጥንቃቄ በጎደለው መጠጋጋት የሚመጣ የሳንባ ምች ተብለው ይከፈላሉ ፡፡

በበሽታው እንደተያዘ የጠረጠረ ሰው ወደ ህክምና ተቋም በመሄድ የደም ምርመራ፣የደረት ኤክስሬይ፣በደም ውስጥ ያለውን የኦክስጅን መጠን በመለካት፣ የአክታ ምርመራ በማድረግ እና በሳንባ አካባቢ ፈሳሽ ቋጥሮ ከሆነ በመርፌ ናሙና ተወስዶ ምርመራ እንዲደረግለት በማድረግ መለየት የሚችል ሲሆን÷ የሳንባ ምቹ ካለበትም አስፈላጊውን ህክምና ማግኘት እንደሚገባም ባለሙያዎች ይመክራሉ፡፡

እንደ በሽታው ክብደት ሁኔታ ሲቲ ስካን እና ብሮንኮስኮፒም ሊታዘዝ እንደሚችልም የኤን አይ ዲ መረጃ ያመላክታል፡፡

በሳንባ ምች የተያዘ ሰው ተገቢውን ህክምና ካገኘ አብዛኛውን ጊዜ ሌላ ጉዳት ሳያስከትል በቀላሉ ሊድን እንደሚችልም ነው ጥናቶች የሚያረጋግጡት ፡፡

Exit mobile version