Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በጎንደርና አካባቢው የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑ ተመላከተ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር እና አካባቢው የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ መሆኑን የጎንደር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ቻላቸው ዳኘው ገለጹ፡፡

በጎንደር ከተማ “ሰላም ለሁሉም፤ ሁሉም ለሰላም” በሚል መሪ ሃሳብ ከሃይማኖት አባቶች ጋር ውይይት ተካሂዷል።

በውይይቱ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው እንዳሉት÷ የእምነት እና አብሮ የመኖር እሴት ባለቤት በሆነችው ጎንደር ባለፈው አንድ ዓመት የማህበረሰቡን ክብር የማይመጥን የጸጥታ ችግር ተስተውሏል።

ነገ ለልጆቻችን የምትመች ሀገር የምናሻግረው ዛሬ ቁርሾ ባለመፍጠር ነው በማለት ገልጸው፤ የተፈጠሩ ስህተቶችን በጥልቅ በመፈተሽ የከተማዋን ሰላም በዘላቂነት መመለስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የገጠመውን የሰላም ችግር ለመፍታት የሃይማኖት አባቶች ሚና የጎላ እንደሆነ ጠቅሰው፤ ከአባቶች ጋር በመመካከር ለሕዝባችን የሚበጅ ዘላቂ ሰላም እንፈጥራለን ነው ያሉት።

ሰላም የሁሉም ነገር መሠረት እንደኾነ የገለጹት የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው÷ የተፈጠረው ችግር ለሀገር እና ለሕዝብ የማይበጅ በመኾኑ ሁሉም ለሰላም እና ለውይይት በአንድነት መቆም እንዳለበት አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላም እንዲፈጠርና የጎንደርን የቆየ ታሪክ የሚያጎድፍ ድርጊት እንዳይደገ የጋራ ጥረት እንደሚያስፈልግ ገልጸው፤ የድርሻቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በሙሉጌታ ደሴ

Exit mobile version