የሀገር ውስጥ ዜና

የቤኑና መንደር ቱሪዝምን ከግብርና ልማት ያጣመረ ውብ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ ነው – አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢሜስበርገር

By Melaku Gedif

November 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የቤኑና መንደር ቱሪዝምን ከግብርና ልማት ያጣመረ ውብ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ መሆኑን በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢሜስበርገር ገለጹ።

ቤኑና መንደር በበሰቃ ሃይቅ ዳርቻ እጅግ ዘመናዊ መኝታ ክፍሎች፣ የስብሰባ አዳራሽ፣ ሲኒማ ቤት፣ መዝናኛ ስፍራ፣ ስፓ እንዲሁም የፍራፍሬ ልማት እና የሌማት ትሩፋትን አካቶ መያዙ ተገልጿል፡፡

የመንደሩ ግንባታም ባህላዊ የኪነ-ህንጻ ጥበብን ከዘመናዊ ግንባታ ጋር አቀናጅቶ በመያዝ ለአካባቢው ማህበረሰብ የመስህብ ልማት ተጨማሪ የቱሪዝም አቅም የፈጠረ መዳረሻ ስፍራ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መንደሩን መርቀው በከፈቱበት ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፣ ቤኑና መንደር ይቻላልን በአይናችን ያየንበት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በዚሁ ጊዜ የተገኙት በኢትዮጵያ የአውሮፓ ሕብረት አምባሳደር ሶፊ ፍሮም-ኢሜስበርገር÷ አካባቢው ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ሃብቶች ተሰናስለው ውብ ገጽታን ያላበሱት አስደናቂ ስፍራ ነው ብለዋል።

በቤኑና መንደር የለማው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርትን ጨምሮ የግብርና ስራዎች ዘላቂ የልማት ግብ መገለጫ ተደርገው የሚወሰዱ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የቤኑና መንደር የተላበሰው ነፋሻማ የአየር ሁኔታም ለቱሪዝም እንቅስቃሴ ምቹ መሆኑን አንስተዋል።

በመንደሩ የብርቱካን፣ የሎሚ፣ የፓፓዬና የማንጎ ልማት እንዲሁም ዶሮ፣ ግመል፣ የከብትና ፍየል እርባታ ልማት ስራን አሰናስሎ በመያዝ ከመዝናኛ ስፍራነት ባሻገር በፍራፍሬና ሌማት ትሩፋት ልማትን በማስተሳሰር ትምህርት የሚወሰድበት ስለመሆኑ ተገልጿል። በኢትዮጵያ መንግስት፣ በግሉ ዘርፍ እና በተባበሩት ዓረብ ኢምሬትስ መንግስት ትብብር ተገንብቶ የተመረቀውን የቤኑና መንደር የስካይ ላይት ሆቴል የማስተዳደር ስራን እንዲያከናውን ሃላፊነት መሰጠቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡