Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኮፕ29 ኢትዮጵያ የደን መልሶ ማልማትና የዘላቂ መሬት አጠቃቀም ተሞክሮዋን ታቀርባለች

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኮፕ29 ኢትዮጵያ በተራቆተ መሬት የደን ሽፋንን መልሶ ለማልማት የወሰደችውን ቁርጠኝነት እና ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀም ተሞክሮዋን እንደምታቀርብ ተገለጸ።

ዓለም አቀፉ የተባባሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ (ኮፕ29) ላይ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ልኡካን ቡድን አዘርባጃን ባኩ ገብቷል።

ጉባኤው የዓለም በካይ ጋዝ ልቀትን መቀነስ፣ ለአየር ንብረት ለውጥ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር ብሎም ዘላቂነት ያለው የአየር ንብረት ለውጥን ማረጋገጥ ላይ ያተኩራል ተብሏል።

የሃይል አቅርቦት ምንጭ፣ የሰብዓዊ ልማት፣ የምግብ ዋስትና እና ብዝሃ-ህይወት የጉባኤው የዚህ ዓመት ትኩረት አቅጣጫ እንደሆኑም ተገልጿል።

ኢትዮጵያ የጀመረቸው የአረንጓዴ አሻራ ልማት ኢኒሼቲቭ በተለይ በግብርና፣ በኢኮ-ቱሪዝምና በታዳሽ ሀይል ላይ እየተሰራ ያለው ስራ የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የተነገረው።

በመሆኑም ኢትዮጵያ በጉባኤው ላይ በተራቆተ መሬት የደን ሽፋንን መልሶ ለማልማት የወሰደችውን ቁርጠኝነት እና ዘላቂነት ያለው የመሬት አጠቃቀም በተሞክሮ ይቀርባል ተብሏል።

የኮፕ 29 ጉባኤ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ጥበቃ ላይ ለምታደረገው አበርክቶ ድጋፍ እና አጋር ለማግኘት ትጠቀምበታለች ተብሎ ይጠበቃል።

በጉባኤው የኢትዮጵያ ልኡክ በታዳጊ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን ለመከላከል የሚያግዝ ድጋፍ እንዲደረግ በትኩረት እንደሚሰራም ነው የተነሳው።

የዘንድሮው የኮፕ 29 ጉባኤ ”በጋራ ለአረንጓዴ ምድር” በሚል መሪ ሀሳብ እየተከናወነ መሆኑን የፕላንና ልማት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል።

Exit mobile version