የሀገር ውስጥ ዜና

በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን ዜጎች ከስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖሩ ተገለጸ

By Melaku Gedif

November 11, 2024

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች ከስኳር ሕመም ጋር እንደሚኖሩ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ቀን በኢትዮጵያ ለ34ኛ ጊዜ ሕዳር 5 ቀን 2017 ዓ.ም በተለያዩ ሁነቶች ይከበራል፡፡

የጤና ሚኒስቴር የበሽታ መከላከልና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት መሪ ሥራ አስፈፃሚ ሕይወት ሰለሞን (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ስኳር ሕመም ማህበር ፕሬዚዳንት ጌታሁን ታረቀ (ዶ/ር) ቀኑን አስመልክተው መግለጫ ሰጥተዋል፡፡

በመግለጫቸውም የስኳር ሕመም አንድ ሰው በደሙ ውስጥ ያለው የስኳር መጠን መሆን ከሚገባው በላይ ከፍ ሲል የሚከሰት መሆኑን አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ሰውነታችን የተመረተውን ኢንሱሊን በአግባቡ መቀበል ሳይችል ሲቀር ወይም ሁለቱም በአንድ ላይ ሲከሰት የስኳር ሕመም እደሚፈጠር አስረድተዋል፡፡

አሁን ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ 653 ሚሊየን ዜጎች ከስኳር ከሕመም ጋር የሚኖሩ ሲሆን÷ በኢትዮጵያ ደግሞ 1 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ ዜጎች ከሕምሙ ጋር እንደሚኖሩ አንስተዋል፡፡

በኢትዮጵያ የስኳር ህመም ካለባቸው ዜጎች ውስጥ 50 በመቶ የሚሆኑት ሕመሙ አንዳለባቸው እንደማያውቁ ጠቁመው÷ ይህም ችግሩን ይበልጥ አስከፊ እንዳደረገው አመልክተዋል፡፡

ስለሆነም ሕብረተሰቡ ጤናማ አመጋገብ በመመገብ፣ ዘወትር የአካል ብቃት እንቅስቃሴ በማድረግ፣ የሰውነት ክብደትን በመቆጣጠር፣ አልኮሆልን ባለመጠጣትና ሲጋራ ባለማጤስ የስኳር ሕመምን መከላከል እንደሚችል አብራርተዋል፡፡

በመላኩ ገድፍ እና አሸናፊ ሽብሩ