Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ያለ ሀገራዊ መግባባት አይጸናም – አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ያለ ሀገራዊ መግባባት እንደማይጸና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር አስገነዘቡ፡፡

19ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል መሪ ሐሳብን በሚመለከት ውይይት እየተካሄደ ነው፡፡

በዚሁ ወቅት አፈ-ጉባዔ አገኘሁ÷ ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መሰረት ነው፤ የወል ትርክቶች ተሰናስለውና ተዋኅደው ሲፈሱ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ይገነባሉ ሲሉ አብራርተዋል፡፡

ዘንድሮም በዓሉን ስናከብር የሕዝቦችን አንድነትና ትስስር እንዲረጋገጥ በማድረግ እንዲሁም የሀገሪቱ ሰላምና አንድነት ተጠብቆ ከእነሙሉ ነጻነቷ ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ጠንክረን በመሥራት ሊሆን ይባል ብለዋል፡፡

ላለፉት 18 ዓመታት በዓሉ ሲከር ሕዝቦች ይዘውት የቆዩትን አብሮነት እንዲያፀኑ እና የጋራ ዕሴቶቻቸውን እንዲያጎለብቱ ዕድል መፍጠሩንም አስረድተዋል፡፡

በዓሉ ትስስር እና አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ የክልሎችና ከተማ መሥተዳድሮች የመሰረተ-ልማት ግንባታዎች እንዲቀጣጠሉ ማድረጉንም አንስተዋል፡፡

“ሀገራዊ መግባባት ለኅብረ-ብሔራዊ አንድነት” በሚል መሪ ሐሳብ የዘንድሮው የብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ቀን በዓል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አርባምንጭ ከተማ እንደሚከበርም ተገልጿል፡፡

በዙፋን ካሳሁን እና ወንድሙ አዱኛ

Exit mobile version