Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ እያስገኛቸው ያሉ ውጤቶች ምንድን ናቸው?

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በተለያዩ ክልሎች እና ከተማ አሥተዳደሮች የሚያከናውናቸውን የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፎች ሲያከናውን መቆየቱ ይታወሳል፡፡

ይህን ተከትሎም የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ እያስገኛቸው ካሉ በርካታ ውጤቶች መካከል የተወሰኑትን ኮሚሽኑ አስታውቋል፡፡

በዚህ ሂደት ኮሚሽኑ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት መሰብሰብ ተቀዳሚ ግቡ መሆኑ ቢታወቅም ሂደቱ ለሀገራዊ ምክክሩ ምዕራፍ ሂደቱ ቀጥተኛ ያልሆነ በጎ አስተዋፅኦን በማበርከት ላይ ነው፡፡

ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሀሳቦች ኮሚሽኑ በሂደቱ እያስመዘገባቸው ያሉ ቀጥተኛ ያልሆኑ ውጤቶች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

  1. በባለድርሻ አካላት መካከል የተሻለ መተማመን እና ግንኙነትን ማዳበር

እየተከናወነ ባለው የአጀንዳ ማሰባሰብ ምክክር ምዕራፍ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ መሳተፍ የሚገባቸው ባለድርሻ አካላት ተገናኝተው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እየመከሩ ይገኛሉ፡፡

ውይይቶቹ በተለያየ ፈርጆች በተለዩ ዜጎች መካከል መተማመንን በመገንባት ተስፋ ሰጪ የሆኑ በጋራ የመስራት ልምምዶች እንዲዳብሩ አስችለዋል፡፡

  1. የባለድርሻ አካላት ባለቤትነትን መፍጠር

የሀገራዊ ምክክር ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባለቤትነት ተሰምቷቸው በሂደቱ በእኩል ሊሳተፉበት የሚገባ የዴሞክራሲ ሂደት ነው፡፡

ሂደቱ በተከናወነባቸው የኢትዮጵያ አካባቢዎች የተለያዩ ባለድርሻ አካላት ለሂደቱ ስኬት በተለያየ ረገድ ያሳዩት ርብርብ እና ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝ ሲሆን÷ ይህም በሂደቱ ያላቸውን ባለቤትነት እንዲገነቡ አስችሏቸዋል፡፡

  1. የምክክር ባህልን ማጎልበት

የአጀንዳ ማሰባሰብ በተከናወነባቸው የተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች ግጭቶችን ሀገር በቀል በሆኑ መንገዶች መፍታት የተለመደ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

ሆኖም ግን በሀገር በቀል የሽምግልና ስርዓት ያልተፈቱ የሀሳብ ልዩነቶችን ለመፍታት ሂደቱ ሀሳቦች በሚገባ እንዲንሸራሸሩ መንገዱን አመቻችቷል፡፡

ይህም የሀሳብ ልዩነት ያላቸው የተለያዩ ጎራዎች በሀሳብ ልዩነቶቻቸው ላይ ተወያይተው የምክክርን ባህል እንዲያጎለብቱ አጋጣሚ ፈጥሯል፡፡

  1. መረጃዎችን ማሰባሰብ

የአጀንዳ ማሰባሰብ የምክክር ምዕራፍ በርካታ የሚባሉ ባለድርሻ አካላትን ማሳተፉ እሙን ነው፡፡

በሂደቱ ኮሚሽኑ ለስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ፍጆታ የሚውሉ እና በቀጣይ ለሚደረጉ የምክክር ሂደቶች ግብዓት የሚሆኑ መረጃዎችን በማሰባሰብ እና በማደራጀት ስኬታማ የሆኑ ተግባራትን አከናውኗል፡፡

Exit mobile version