አዲስ አበባ፣ ሕዳር 2፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በመንግሥት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ ሁሴን አስገነዘቡ፡፡
የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽን ከባለድርሻ አካላት ጋር ተፈናቃዮችን በዘላቂነት ማቋቋም በሚቻልበት ሁኔታ ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡
የኮሚሽኑ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በዚሁ ወቅት÷ የመድረኩ ዓላማ በክልሉ በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ የአንድ ተቋም ኃላፊነት ብቻ ተደርጎ መወሰድ እንደሌለበትም በዚሁ ወቅት መገለጹን የኮምቦልቻ ከተማ ኮሙኒኬሽን ጽሕፈት ቤት መረጃ አመላክቷል፡፡
ተፈናቃዮችን በዘላቂነት የማቋቋም ሥራ በትኩረት እና በዕቅድ መሠራት እንደሚኖርበት ያነሱት በምክትል ርዕሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ልማት ዘርፍ አስተባባሪና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ድረስ ሳኅሉ (ዶ/ር)÷ ከተረጂነት ስሜትና ፍላጎት ለመውጣት ቁርጠኛ በመሆን ተፈናቀዮችን ወደ አካባቢያቸው መመለስ ይገባል ብለዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መሥተዳድር አብዱ በበኩላቸው በተለያዩ ምክንያቶች የተፈናቀሉ ዜጎችን በዘላቂነት ለማቋቋም የሚደረገው ጥረት በመንግሥት ብቻ ውጤታማ ስለማይሆን በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡