Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎቹ የመንግሥት ጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ናቸው- የአፍሪካ ነጻ ንግድ ሴክሬታሪ ዋና ፀሐፊ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ እያየናቸው ያሉት የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎች መንግሥት እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ናቸው ሲሉ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ሴክሬታሪ ዋና ፀሐፊ ዋምከሌ የማኔ ገለጹ፡፡

በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በተካሄደው 15ኛው የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ሚኒስትሮች ጉባዔ ለተሳተፉት እንግዶች የእራት ግብዣ ተካሂዷል፡፡

የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒትስር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፥ የአፍሪካ አኅጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና የአፍሪካን ንግድ ከማሳደግ በዘለለ አኅጉራችን በዓለም ገበያ ውስጥ ተወዳዳሪ እንዲሆን ያርጋል ብለዋል፡፡

የነጻ ንግድ ስምምነቱ የሸቀጦችና አገልግሎቶች አንድ ገበያ በመፍጠር ኢኮኖሚያዊ ውኅደትን ለማጎልበት የሚያስችል መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ዋምከሌ የማኔ በበኩላቸው÷ 15ኛውን የአፍሪካ ነፃ ንግድ ቀጣና ሚኒስትሮች ጉባዔ ኢትዮጵያ ውስጥ ማካሄዳችን በጣም ትክክል ነበር ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ላደረገልን መስተንግዶም እናመሠግናለን ማለታቸውን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡

በአዲስ አበባ ዛሬ የምናያቸው የመሰረተ-ልማት ዝርጋታዎች በሙሉ መንግሥት እያካሄደ ያለው ጥልቅ ተሃድሶ ውጤት ማሳያ ናቸው ብለዋል፡፡

እነዚህ ማሻሻያዎችም ከአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ዓላማዎች ጋር የሚጣጣሙ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ይህም ኢትዮጵያ የሥራ እድል ፈጠራና የፈጠራ ስራዎችን እንድታሳድግ ብሎም ተወዳዳሪና የኢንዱስትሪ ማዕከል እንድትሆን ያስችላል ነው ያሉት፡፡

የጉባዔው ተሳታፊዎች በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚገኘውን የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ማዕከል እና በገላን የሚገኘውን “ኤ ኤም ጂ የቡናና የብረታብረት ፋብሪካ ጎብኝተዋል፡፡

 

Exit mobile version