Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የሀገራችንን ብልጽግና እውን ለማድረግ በትጋት እንሠራለን- አቶ ሽመልስ አብዲሳ

አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገራችን መሠረታዊ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ በማምጣት ብልጽግናን እውን ለማድረግ በትጋት እንሠራለን ሲሉ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መሥተዳድር ሽመልስ አብዲሳ ገለጹ፡፡

አቶ ሽመልስ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ÷ የሀገራችንን የኋላ ቀርነት ታሪክ ከሁሉም በላይ ከኢኮኖሚያዊ ችግሮች የሚመነጨውን ለመቅረፍ የለውጡ መንግሥት ጠንከር ያሉ ርምጃዎችን በመውሰድ በፍጥነት እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

በዚሁ መሠረት ሁሉን አቀፍ የሆነ ኢኮኖሚ ለመገንባት በተያዘውን ዕቅድ፣ የቱሪዝም ሴክተር እንደ አንድ የትኩረት አቅጣጫ ተይዞ ፈጣን ለውጥ እያስመዘገበ ይገኛል ነው ያሉት፡፡

የቱሪዝም ሴክተር ሰፊ እምቅ አቅም ያለውና ለሀገራችን ትልቅ ውጤት የሚያስገኝ ሆኖ ሳለ የማልማቱ ስራ ለዘመናት ትኩረት ተነፍጎት ቆይቷል ሲሉም አስታውሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ (ዶ/ር) የላቀ የፖሊሲ አቅጣጫ ወደ ሥራ ከተገባ በኋላ በአስገራሚ አፈጻጸም ሀገራችን በዚህ ረገድ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እውን የሚያደርግ ስራ በስፋት እየተከናወነ ነው ብለዋል፡፡

ለአብነትም በምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ በሰቃ ሐይቅ ዙሪያ ተደብቆ የኖረው ውበት ብርሃን አግኝቷል ያሉት አቶ ሽመልስ÷ ይህ አፈጻጸም ከማይናወጥ የሀገር ትልምና ዓላማ ተኮርነት የመነጨ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል፡፡

በቀጣይም ለሀገራችን መሠረታዊ ችግሮች መሠረታዊ መፍትሔ በማምጣት ብልጽግናን እውን ለማድረግ ጠንክረን እንደምንሠራ አረጋግጣለሁ ነው ያሉት፡፡

በበሰቃ ሐይቅ ዙሪያ የተከናወነውን ሥራ ለማሳካት አስተዋጽኦ ላበረከቱ የአመራር አባላትና ባለድርሻ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል፡፡

Exit mobile version