አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ለፍሬምናጦስ የአረጋዊያን፣ የህፃናትና የአእምሮ ሕሙማን ማዕከልን ለመደገፍ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ የሩጫ ውድድር በመቐለ ከተማ ተካሂዷል።
የሩጫ ውድድሩን ያስጀመሩት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ርዕሰ መስተዳድር ጌታቸው ረዳ÷ማዕከሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ለአገልግሎት እንዲበቃ መላው የክልሉ ህዝብ ድጋፉን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል።
ለማዕከሉ ግንባታ መጠናቀቅ የሁሉንም ትብብር የሚሻ ነው ያሉት አቶ ጌታቸው÷በክልሉ የሚገኙ ባለሃብቶችና የመንግስት ተቋማት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
የማዕከሉ መስራች አባ ገብረ መድህን አስገዶም በበኩላቸው÷የሩጫ መርሐ ግበሩ በማዕከሉ ለሚገኙ ወላጅ ለሌላቸው ህፃናት፣ ተንከባካቢ ለሌላቸው አረጋውያን እንዲሁም ለአዕምሮ ሕመምተኞች አዲስ ማዕከል ለመገንባት ያለመ መሆኑን ገልጸዋል።
”ማዕከሉን ለመገንባት ከ3 ቢሊየን ብር በላይ እንደሚያስፈልግ ጠቁመው÷ማዕከሉ የመኖሪያ፣ የሆስፒታል፣ የትምህርት ቤት፣ የመዝናኛ ማዕከላት እና መሠል ህንጻዎችን ያጠቃለለ እንደሆነም ጠቁመዋል።
የማዕከሉ ግንባታ ተጀምሮ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ በህብረተሰቡና በመንግስት የተጀመረው እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል መጠየቃቸውንም ኢዜአ ዘግቧል፡፡