አዲስ አበባ፣ ሕዳር 1፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የጎግል ፕሌይ (Google Play) አልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩን የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር)÷የጎግል ፕሌይ የአልሚዎች ምዝገባ ኢትዮጵያውያን አልሚዎችን መቀበል መጀመሩ ለኢትዮጵያ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ትልቅ ተጽዕኖ የሚፈጥር ነው ብለዋል፡፡
ይህ ምዕራፍ የሀገር ውስጥ የቴክኖሎጂ ተሰጥኦ ባለቤቶች መተግበሪያዎቻቸውን በዓለም ካሉት ትላልቅ ዲጂታል መድረኮች ላይ እንዲያትሙ አዲስ እድሎችን እንደሚከፍት አንስተዋል፡፡
መንግስት የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለመገንባት በርካታ ተነሳሽነቶችን በመተግበር እየሰራ መሆኑን ጠቁመው÷ ይህ አዲስ ጅማሮ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት ነው ብለዋል።
ይህንን እድል ተጠቅመው የዘርፉ ባለሙያዎች ችግር ፈቺ መተግበሪያዎችን በማልማት በዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታ ሒደት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ጥሪ ማቅረባቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡
እድሉ ኢትዮጵያውያን አልሚዎች የጎግል ፕሌይን ዓለም አቀፍ ታዳሚዎች በቀጥታ በማስገኘት መተግበሪያዎቻቸው ሰፊ እይታን እንዲያገኙና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንዲሆን እንደሚያግዝ ተጠቁሟል፡፡