ጤና

በደቡብ ወሎ ዞን ከ32 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባ ጤና ጣቢያ ተመረቀ

By Shambel Mihret

November 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ኩታበር ወረዳ ከ32 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ የተገነባ የመለስተኛ ቀዶ ጥገና አገልግሎት መስጠት የሚችል ጤና ጣቢያ ተመርቋል።

በዚሁ ወቅት የክልሉ ጤና ቢሮ ሀላፊ ዶክተር አብዱልከሪም መንግስቱ÷በክልሉ የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለማስጠበቅ በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ነው ብለዋል፡፡

በተለይ የእናቶችን እና ህፃናትን ጤና ለመጠበቅና አንድም እናት በወሊድ ምክንያት ህይወቷን እንዳታጣ በክልሉ ካሉ ከ923ቱ የጤና ጣቢያዎች በመለስተኛ ደረጃ በቀዶ ጥገና የማዋለድ አገልግሎት የሚሰጡ 117 ጤና ጣቢያዎች መኖራቸውን ገልጸዋል፡፡

ሌሎች 104 ጤና ጣቢያዎችም ግንባታቸው ተጠናቆ 19 ጤና ጣቢያዎች የመለስተኛ ቀዶ ሕክምና አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውንም አንስተዋል።

የእናቶችና ህፃናትን ሞት መቀነስ የሚቻለው የጤና መሰረተ ልማቱን ተደራሽ በማድረግ መሆኑን ያነሱት ሃላፊው መለስተኛ የቀዶ ጥገና አገልግሎት የሚሰጡ ጤና ጣቢያዎችን መገንባት ብቻ ሳይሆን ማሟላት ያለባቸውን ትልልቅ የህክምና መሳሪያዎች ማሟላት መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ለዚህም አክሲሲ ከተባለ መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት ጋር እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷ በደቡብ ወሎ ዞን ብቻ ስድስት የጤና ጣቢያዎች መለስተኛ የሆነ የቀዶ ጥገና አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በስንታየሁ አራጌ