የሀገር ውስጥ ዜና

“The Green Legacy” ዘጋቢ ፊልም በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ ሊቀርብ ነው

By Feven Bishaw

November 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአረንጓዴ አሻራ የተገኙ ውጤቶችን የሚያሳየው “The Green Legacy” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ዘጋቢ ፊልም ከዛሬ ጀምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲቀርብ መመረጡን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊ ቢልለኔ ስዩም ገለጹ።

የፕሬስ ሴክሬታሪያት ኃላፊዋ እንዳሉት÷ ኢትዮጵያ በ2011 ዓ.ም በተጀመረውና ታላቅ ግብ በሰነቀው የአረንጓዴ አሻራ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር ላይ ስትሰራ ቆይታለች።

በቅርቡ የተለቀቀው የደን ሽፋን ሪፖርት አስደናቂውን ውጤት ይፋ ማድረጉን ጠቅሰው በዚህም የኢትዮጵያ የደን ሽፋን በ2011 ዓ.ም ከነበረበት 17 ነጥብ2 በመቶ ወደ 23 ነጥብ 6 በመቶ ከፍ ማለቱን አመልክተዋል።

ይህን ታሪካዊ ክንውን በማስመልከት የተሰራውና በሰኔ 2016 ዓ.ም ለእይታ የበቃው “The Green Legacy” የተሰኘው ዓለም አቀፋዊ ዘጋቢ ፊልም የዚህን ሀገራዊ ጥረት ውጤቶች ማሳየቱን ተናግረዋል።

ፊልሙ መሳጭ በሆኑ ግለሰባዊ ተረኮች ላይ ተመስርቶ የአረንጓዴ አሻራ ሥራ የኢትዮጵያን መልክዓ ምድር እና ሥነ ምኅዳር እንዴት እንደቀየረው ብሎም የሕዝቦችን ሕይወት እንዳበለፀገው መግለጹን አስረድተዋል።

ፊልሙ ከዛሬ ጀምሮ በሚቀጥሉት ወራት የሚከተሉትን ጨምሮ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎች ላይ እንዲቀርብ መመረጡን ኃላፊዋ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ገልጸዋል።

ፊልሙ ለዕይታ የሚቀርብባቸው ዓለም አቀፍ የፊልም ፌስቲቫሎቹም ፦ 1) Bridge for Peace Festival in France for Best Documentary — November 9, 2024 2) Africa USA International Film Festival — November 17, 2024 3) Logo Lumina Flicks International Short Film Festival in Albania — December 26, 2024 4) Cinemaking International Film Festival in Bangladesh — December 26, 2024 መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡