Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ለደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር እየተካሄደ ነዉ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በደሴ ከተማ በመንግሥት እና በኅብረተሰብ ተሳትፎ ለሚሰራው የኮሪደር ልማት የገቢ ማሰባሰቢያ መርሐ ግብር በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ነዉ።

በመርሐ ግብሩ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባና የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ ዣንጥራር ዓባይን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

አቶ አረጋ ከበደ በመርሐ ግብሩ ላይ እንዳሉት፤ ደሴ ከተማ ያላትን የተፈጥሮ ሃብት በመጠቀም ማልማት ያስፈልጋል።

ከተማዋን ለማስዋብ የኮሪደር ልማት ስራ መጀመሩን ጠቅሰው፤ ደሴን ማልማት የክልሉን ሃብት ይበልጥ መደገፍ መሆኑን አስገንዝበዋል።

በመሆኑም በዚህ ታሪካዊ ተግባር ሁሉም እንዲሳተፍ ጥሪ ማቅረባቸውን አሚኮ ዘግቧል።

የአብሮነትና የመቻቻል ተምሳሌት የሆነችዉን ደሴ ከተማን ለማልማት የመጣችሁ ምሥጋና ይገባችኋል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አሥተዳደር ምክትል ከንቲባና የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት አስተባባሪ ዣንጥራር ዓባይ በበኩላቸዉ ደሴ እንደ ቀደምትነቷ መልማት እንደሚገባት ገልጸው፤ ይህንን ልማት የመደገፍ ኃላፊነት የሁሉም ሃላፊነት እንደሆነ ተናግረዋል።

የደሴ ከተማ የኮሪደር ልማት መንገድ፣ የታክሲ ተርሚናሎች፣ የመዝናኛ ቦታዎች፣ የወንዝ ዳርቻ መሰረተ ልማት እንዲሁም የመኪና ማቆሚያ ቦታዎችን ያካተተ ሲሆን፤ ይህንን ለማጠናቀቅ ከ1 ቢሊዮን ብር በላይ ያስፈልጋል።

Exit mobile version