Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገራችን ሉዓላዊነትና በሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው – አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን 

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገራችን ሉዓላዊነትና በሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ሲሉ የብሔራዊ መረጃ እና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ገለጹ።

አምባሳደር ሬድዋን ለመከላከያ አዛዥነትእና ስታፍ ኮሌጅ ተማሪዎች አመራሮች እና መምህራን በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ገለጻ አድርገዋል።

በገለጻቸውም ከሁሉም ሀገራት ጋር ሰላምን እና ብሔራዊ ጥቅምን ያስቀደመ ስራ እየተሰራ እንደሚገኝ አንስተው፤ ይህንኑ አጠናክሮ በማስቀጠል ኢትዮጵያ ያላትን ተሰሚነት አስጠብቆ ማስኬድ ተችሏል ብለዋል።

ጎረቤት ሀገራትን በማስቀደም አጋርነትን በማስፋት፣ በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊ እና በደህንነት ጉዳዮች ዙሪያ በትብብር መስራት የሚያስችል ፖሊሲ ተቀርጾ እየተሰራበት እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የውስጥ ሰላምና አንድነት፣ የሰከነ ማህበራዊና ፖለቲካዊ መስተጋብር ዋናው የጥንካሬ ምንጭ ነው ያሉት አምባሳደር ሬድዋን፤ ይህንን ለማረጋገጥ ብሄራዊ መግባባትን፣ ድህነትን መቅረፍና አካታችና ፍትሃዊ እድገት፣ እየተለወጠ የመጣውን ዓለማዊ ሁኔታ ታሳቢ ያደረገ ወትሮ ዝግጁነት እውን ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል።

ለዚህም የአስር ዓመት መሪ እቅድ መዘጋጀቱን፣ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መቀረፁንና ለመጀመሪያ ጊዜ ራሱን የቻለ የብሄራዊ ደህነት ፖሊሲ ቀረፃም በመጠናቀቅ ላይ እንደሆነ ጠቁመዋል።

ያለ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊትና የደህንነት ተቋማት አስተማማኝ ሰላም ማስፈንና ብሄራዊ ጥቅምን መከላከል አዳጋች እንደሆነ አስገንዝበው፤ እየተገነባ የሚገኘው የመከላከያ ኃይል ለሀገራን ሉዓላዊነት እና በሔራዊ ጥቅሞች መረጋገጥ ዋስትና ነው ሲሉ ገልጸዋል።

በሁሉም ዘርፍ የህዝቦችን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እና ውስጣዊ አንድነትን ለማጠናከር መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ መግለጻቸውን የመከላከያ ሰራዊት ማህበራዊ ትስስር ገጽ መረጃ አመልክቷል።

የመከላከያ አዛዥነትእና ስታፍ ኮሌጅ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ሙሉጌታ አምባቸው በበኩላቸው የመከላከያ ሰራዊታችንን ወታደራዊ አመራሮች አቅም ለማሳደግተከታታይነት ያላቸው ስልጠናዎች እየተሰጡ ይገኛሉ ብለዋል።

Exit mobile version