አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥና ድህነትን ለመቀነስ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ወሳኝ ነው ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ገለፁ፡፡
15ኛው የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ በአዲስ አበባ አፍሪካ ህብረት አዳራሽ እየተካሄደ ነው።
በመክፈቻ ስነ ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ታዬ አጽቀ ሥላሴ÷ የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና ሀገራቱን ለማቀራረብና በንግድ ለማስተሳሰር ትልቅ አቅም እንዳለው ገልጸዋል።
በአህጉሪቱ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ፣ ድህነትን ለመቀነስና የጾታ እኩልነትን ለማምጣት ትልቅ ድርሻ ያለው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በአፍሪካ የታሰበውን ጠንካራ ኢኮኖሚ ለመገንባትም በየሀገራቱ ያለውን የተበጣጠሰ የንግድ እንቅስቃሴ በአንድ የንግድ ስርዓት ማስተሳሰር እንደሚያስፈልግ ገልጸው÷ ኢንዱስትሪዎችን ማስፋፋትና ቴክኖሎጂን መጠቀም ላይ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል።
የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በበበኩላቸው ጉባኤው አፍሪካን በጋራ ውጤታማ የሚያደርጉ አቅጣጫዎችን ለማመላከት፣ ችግሮችን ለመፍታትና ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ለመምከር እንደሚያስችል ገልጸዋል።
ኢትዮጵያ የግል ዘርፉን ተሳትፎ፣ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት እና ዲጂታል ትራንስፎርሜሽንን በማበረታታት እድገት ተኮር የኢኮኖሚ ሪፎርም እያካሄደች መሆኑን ገልጸው፤ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና የአገልግሎት እና የእቃዎች ንግድ አንድ የጋራ ገበያ ለመፍጠር ከፍተኛ እድል ማምጣቱን ተናግረዋል።
በአባል ሀገራት መካከል ንግድን በማሳለጥ፣ ኢንዱስትሪያላይዜሽንን በመገንባት ሰፊ ዕድል የሚፈጥር ነው ያሉት ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ለሚካሄዱ ማንኛውም ትብብሮች ከአባል ሀገራት ጋር በመቆም የበኩሏን እንደምትወጣ አረጋግጠዋል።
በታሪኩ ለገሰ