Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የአዲስ አበባ ፖሊስ ያከናወናቸው የለውጥ ስራዎች ፍሬያማ መሆናቸውን ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት እንደ ተቋም ያከናወናቸው የለውጥ ስራዎች ፍሬያማ መሆናቸውን አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ በ2016 በጀት ዓመት የተሻለ የስራ አፈፃፀም ላስመዘገቡ አመራሮች፣ አባላት እንዲሁም ለተልዕኮው መሳካት ጉልህ ሚና ለነበራቸው አካላት የዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር እያካሄደ ነው።

በመድረኩ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው ባደረጉት ንግግር፤ ሀገራዊ የለውጥ ስራውን ተከትሎ የፀጥታ እና ደህንነት ዘርፉ ትልቅ ለውጥ የታየበት መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባ ፖሊስም ቴክኖሎጂን በመታጠቅ፣ የዜጎችን ደህንነት በመጠበቅ እና የተለያዩ ስራዎች በመተግበር ረገድ ስኬት ማስመዝገቡን ተናግረዋል።

የመዲናዋን ሰላምና ደህንነት ከመጠበቅ አኳያም ሕዝባዊ እና ኃይማኖታዊ በዓላት ያለ አንዳች የፀጥታ ስጋት በሰላም ተከብረው ማለፋቸው አስታውሰዋል።

በፅንፈኛው ኃይል የታቀደ የሽብር ድርጊት ማክሸፍ መቻሉ የዚህ ማሳያ ስለመሆኑም አመልክተዋል።

በዚህም የ2016 በጀት ዓመት የለውጥ ስራ ውጤት የታየበት እንደሆነ ገልጸዋል።

ለዚህ ስኬት ተቋማት፣ ባለድርሻ አካላት እና መላው ነዋሪ የላቀ ሚና እንደነበራቸው ጠቁመው፤ የለውጥ ስራዎቹ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

በወንድሙ አዱኛ

Exit mobile version