የሀገር ውስጥ ዜና

በአማራ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች እየተተገበረ መሆኑ ተገለጸ

By Mikias Ayele

November 09, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 30፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል በሚገኙ የጤና ተቋማት የላቦራቶሪ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞች እየተተገበረ መሆኑን የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።

ኢንስቲትዩቱ “ጥራት ያለው የላቦራቶሪ አገልግሎት ለማይበገር የጤና ሥርዓት” በሚል መሪ ሃሳብ ያዘጋጀው ፌስቲቫል በባሕር ዳር ከተማ እየተካሄደ ነው።

ፌስቲቫሉ የኅብረተሰብ ጤና አደጋዎችን በወቅቱ በመለየት ተላላፊ እና ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎችን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ያለውን አቅም ለማሳደግ ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ፌስቲቫሉ በክልሉ በሁሉም የጤና ተቋማት የሚገኙ የዘርፉ ባለሙያዎች የላቦራቶሪ አገልግሎታቸው ላይ በመምከር የተሻለ አገልግሎት እንዲፈጠር እንደሚያስችል ተመላክቷል፡፡

በተጨማሪም በፌስቲቫሉ የሕክምና ውሳኔዎችን ውጤታማነት በማሻሻል የውሳኔ አሰጣጥ ሂደቱን የሚያሳልጥ ከመሆኑ በላይ ለጤና ፖሊሲ አውጪዎችና ለጤና ዘርፍ መሪዎች ትልቅ አዎንታዊ ሚና አለው ተብሏል።

የክልሉ ኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በክልሉ በሚገኙ ጤና ተቋማት የተለያዩ የላቦራቶሪ የጥራት ማሻሻያ ፕሮግራሞችን እየተገበረ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

ኢንስቲትዩቱ በዓለም አቀፍ የላቦራቶሪ አገልግሎት የጥራት ማረጋገጫ መስፈርት አይ ኤስ ኦ ከ 2011 ዓ.ም ጀምሮ እውቅና የተሰጠው የላቦራቶሪ አገልግሎት እየሰጠ መሆኑ ተገልጿል።

በደሳለኝ ቢራራ