አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስምምነት ማዕቀፍን መተግበር የሚያስችል ቁመና ላይ መሆኗን ተገንዝበናል ሲሉ የ19ኛው የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ስብሰባ ተሳታፊዎች ገለጹ።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ ንግድ ቀጣና ስምምነት አባል ሀገራት 19ኛው የከፍተኛ የንግድ ኃላፊዎች ጉባዔ ተሳታፊዎች የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ ማሳያ ኤግዚቢሽን ማዕከልን ጎብኝተዋል።
በማዕከሉ የግብርና ምርቶች፣ የኢንዱስትሪ ምርቶች ማዕድንን ጨምሮ ወደ ውጭ የሚላኩ ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ ለጎብኚዎቹ ገለጻ ተደርጎላቸዋል።
ከጎብኚዎቹ መካከል የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና የቡሩንዲ ተወካይና ዋና ተደራዳሪ ኦኒዚሜ ኒዩኩሪ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት÷ በጉብኝቱ የንግድና የአገልግሎት ዘርፉ ለኢትዮጵያ ዕድገት ምን ያህል አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን መገንዘብ ችያለሁ ብለዋል።
ኢትዮጵያ በግብርና፣ በአምራች ዘርፍና በሌሎች መስኮችም የደረሰችበትን ደረጃ ማወቅ መቻላቸውን ገልጸው÷ መሰል ቋሚ ኤግዚቢሽን የውጭ ኢንቨስተሮችን በመሳብ ረገድ ዘርፈ ብዙ ፋይዳ አለው ነው ያሉት።
በኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን ለመተግበር የሚደረጉ ዝግጅቶችን ተዘዋውሬ ጎብኝቻለሁ ያሉት ዋና ተደራዳሪው÷ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ነጻ ንግድ ቀጣና ሥምምነትን መተግበር የሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
የላይቤሪያ ንግድ ሚኒስቴር ተወካይ ሪቻርድ ፕራት በበኩላቸው÷ በማዕከሉ የጎበኘናቸው ምርቶች ኢትዮጵያ ሌሎችም የአፍሪካ ሀገራት ሰፊ የገበያ መዳረሻ መሆን የምትችል ሀገር መሆኗን የሚያመላክቱ ናቸው ብለዋል።
የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጣናን እውን ለማድረግ በሚደረገው እንቅስቃሴ ኢትዮጵያ ምሳሌ የሚሆን ሥራ እያከናወነች መሆኑን አይተናል፤ ለሌሎች ሀገራትም አርአያ የሚሆን ነው ሲሉ ተናግረዋል። የአፍሪካ ሀገራት ከሥምምነት ማዕቀፉ ተገቢውን ጥቅም እንዲያገኙ የእርስ በእርስ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸውም አመልክተዋል።
የኬንያ ተወካይ ፊቢያን ሞታማ በበኩላቸው÷ አብዛኛው የአፍሪካ ሀገራት ምርቶችን ከውጭ ነው የሚያስገቡት፤ ይህ ሁኔታ መቀየር አለበት ሀገራት በራስ አቅም ማምረት ላይ ትኩረት ሊያደርጉ ይገባል ብለዋል።
ኢትዮጵያም በዚህ ረገድ አርዓያ የሚሆን ሥራ እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው÷አህጉራዊ አጀንዳ 2063 እውን እንዲሆን ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን መገንዘባቸውንም ለኢዜአገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ደኤታ ያስሚን ወሃብረቢ ÷የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና ሥምምነት ማዕቀፍ እውን እንዲሆን ኢትዮጵያ ከመጀመሪያው ጀምሮ ስትሰራ መቆየቷን አስታውሰዋል።
የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ ንግድ ቀጣና 15ኛው የንግድ ሚኒስትሮች ስብሰባ የፊታችን ቅዳሜና እሑድ በአዲስ አበባ እንደሚካሄድ ይጠበቃል።