አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አመራሩ የአገልጋይነት መንፈስን ተላብሶ የማህበረሰቡን ጥያቄ ለመመለስ በትኩረት ሊሰራ ይገባል ሲሉ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ ገለፁ።
የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የመጀመሪያ ሩብ ዓመት እቅድ አፈፃፀም ግምገማ መድረክ ሲጠናቀቅ ርዕሰ መስተዳድሩ እንዳሉት÷ በሐረሪ ክልል በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ የልማት ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ፡፡
የማህበረሰቡን የልማት እና የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመቅረፍ አመራሩ ለህዝብ ጥያቄ ቅድሚያ በመስጠት በአገልጋይነት መንፈስን ሥራዎችን ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የህዝብን ችግር የመቅረፍ ስራ ቅድሚያ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ጠቁመው÷ ለዚህም አገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻል የተቋማትን የማስፈፀም አቅም የማሳደግ ሥራ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልፀዋል።
በተለይ በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ ማነቆ የሆኑ የሌብነት፣ ብልሹ አሰራሮች እና የመልካም አስተዳደር ችግር የሚታይባቸውን ተጠያቂ ለማድረግ እንደሚሰራ ጠቁመዋል።
የመንግስት ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን ፈጣን፣ ቀልጣፋ፣ ነፃ እና ፍትሃዊ በማድረግ የመልካም አስተዳደርን ዕውን ለማድረግ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡
በሌላ በኩል በመጀመሪያው ሩብ ዓመት በሁሉም ዘርፎች የተመዘገቡት አበረታች ውጤቶችን በተሻለ ፍጥነት እና የጥራት ደረጀ እንዲከናወኑ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል።
በቀጣይ ጊዜያት የከተማ ግብርና እና የሌማት ትሩፋት በክልሉ በልዩ ትኩረት የሚሰሩ ስራዎች እንደሆኑ መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመላክታል፡፡
በስራ ዕድል ፈጠራ፣ ኢንቨስትመንት እና ቱሪዝም ዘርፍ ያሉ ውስንነቶችን በመቅረፍ ውጤታማ ስራ በመስራት የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።
በክልሉ ገቢራዊ እየሆነ የሚገኘውን የኮሪደር ልማት ስራ በማስፋት የማህበረሰቡን የመሰረተ ልማት ጥያቄ ለመመለስ እንደሚሰራ እና በተመረጡ የተጎሳቆሉ አካባቢዎች የመልሶ ልማት ሥራዎች እንደሚከናወን ጠቁመዋል።