አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአጭር ጊዜ በምግብ ራሳችን በመቻል ለዓለም ተምሳሌት ሀገር እንሆናለን ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታወቀ።
አገልግሎቱ ባወጣው መግለጫ፤ አሁን የታዩ አበረታች ውጤቶችን በማስቀጠል ከምግብ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀን ራሳችን መቻል ሉዓላዊነታችንን የተሟላና የፀና ያደርገዋል ብሏል።
በአባቶቻችን ተጠብቆ የቆየ ሉዓላዊነታችን በጀግኖች አርሶ አደሮቻችን፣ በየእርከኑ ባሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ላብ ሉዓላዊነታችን ፀንቶ ይቀጥላል በማለት ገልጾ፤ በአጭር ጊዜ በምግብ ራሳችን በመቻልም ለዓለም ተምሳሌት ሀገር እንሆናለን ሲል አስታውቋል።
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ያወጣው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
በደማችን ተከብሮ የቆየው ሉዓላዊነታችን በላባችን ፀንቶ ይቀጥላል!
ኢትዮጵያ በተለያዩ ወቅቶች በውጭ ወራሪዎችና ጠላቶች የሚቃጡባትን ጥቃቶች በጀግኖች ኢትዮጵያዊያን ደምና አጥንት ሉዓላዊነቷ ተከብሮ፣ የነፃነት ተምሳሌት ሆና ኖራለች፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያ የቀደምት ስልጣኔዎች ባለቤት፣ በተፈጥሮ ሀብቶች የበለጸገች፣ የሰው ልጅ እና የቡና መገኛ፣ በቅኝ ያልተገዛች የነፃነት ተምሳሌት ናት፡፡
ይሁን እንጂ ይህ አኩሪ ታሪካችንና ማንነታችን በተለያዩ ውስብስብ ምክንያቶች በኢኮኖሚያዊ እድገታችን ከዓለም ሀገራት ወደኋላ ቀርተናል፡፡ ይህ ሄኔታ ወደኋላ መቅረት ብቻም ሳይሆን በስንዴ ምፅዋት እንድንኖር አድርጎናል፡፡ በአባቶቻችን ደምና አጥንት ተጠብቆና ተከብሮ የኖረው ሉዓላዊነታችን በላባችን ማፅናት ባለመቻላችን በስንዴ ልመና እና እርዳታ ነፃናታችን ተሸራርፏል፡፡ ሕዝቡን ለመመገብ የሌለውን እጅ የሚጠብቅ ነፃነቱና ሉዓላዊነቱ የተሟላ አይሆንምና፡፡
በመሆኑም ይህንን የእርዳታ ጥገኝነት ሁኔታን ለመቀየር፣ “በደም የተጠበቀውን ሉዓላዊነት በላባችን እናፀናል” በሚል ቁርጠኛ አቋምና ርዕይ በምግብ ራስን ለመቻል ተግባራዊ እርምጃዎችን መውሰድ ተጀምሯል፡፡ በምግብ እህል ራሳችንን ለመቻል በልዩ ትኩረት መስራት ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ መጥተዋል።
ቁርጠኝነት በተሞላበት የመንግሥት አቅጣጫን በመከተል ሀገሪቱ በአጭር ጊዜ ውስጥ በስንዴ ምርት ራስን ለመቻል በተደረገው ርብርብ ሀገራችን ስንዴን ከመሸመት ወጥታ ለውጭ ገበያ ማቅረብ ጭምር ችላለች፡፡ በዘርፉ በተመዘገበው ውጤት እውቅናና ሽልማትም ተችሯታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በምግብ ራስን ለመቻል ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ተጀምሯል፡፡
በተለይም ባለፉት ሦስት እና አራት ዓመታት የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር፣ የበጋ ስንዴ፣ የሌማት ትሩፋትና መሰል ስኬታማ ንቅናቄዎች በምግብ ራስን ለመቻል የተደረጉ ጥረቶች ማሳያዎች ናቸው፡፡ በመስኖ በሚለማ የበጋ ስንዴ ምርት አስደናቂ እመርታ በማስመዝገብ ከውጭ በሚገቡ ምርቶች ላይ ያለውን ጥገኝነት በእጅጉ በመቀነስ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ዶላር ወጪን ማዳን ተችሏል። በአትክልትና ፍራፍሬ ልማትም ራስን ከመቻል ባሻገር እንደ አቮካዶ ያሉ ምርቶችን ለዓለም ገበያ ማቅረብ ጀምረናል፡፡
በግብርናዉ ዘርፍም ቴክኖሎጂ እና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ግብዓቶችን መጠቀም መጀመራችን ይበልጥ መደላድልን ፈጥሯል፡፡ ለዚህ አመቺ መደላድል ለመፍጠርም የግብርና ቴክኖሎጂዎች ከቀረጥ ነፃ የሚገቡበት የሕግ ማሻሻያ በለውጡ ማግሥት ተደርጓል፡፡ እንደ አፈር ማዳበሪያ ያሉ ግብዓቶችም በበርካታ ቢሊዮን ብር የመንግሥት ድጎማ ለአርሶ አደሩ እየቀረቡ ይገኛል፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከዓለማችን በግብርና ምርት ፈጣን ለውጥ ካመጡ ሀገራት መካከል በግንባር ቀደምትነት ትጠቀሳለች።
አሁን የታዩ አበረታች ውጤቶች በማስቀጠል ከምግብ እርዳታ ጥገኝነት ተላቀን ራሳችን መቻል ሉዓላዊነታችንን የተሟላና የፀና ያደርገዋል፡፡ በአባቶቻችን ተጠብቆ የቆየ ሉዓላዊነታችን በጀግኖች አርሶ አደሮቻችን፣ በየእርከኑ ባሉ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና በሌሎች ባለድርሻ አካላት ላብ ሉዓላዊነታችን ፀንቶ ይቀጥላል፡፡ በአጭር ጊዜ በምግብ ራሳችን በመቻልም ለዓለም ተምሳሌት ሀገር እንሆናለን፡፡
ሰሞኑን ኢትዮጵያ ከረሃብ ነፃ ዓለም ጉባኤን የማስተናገዷ አንዱ ምሥጢርም በግብርናዉ ዘርፍ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ያስመዘገበችዉ ስኬት ነው፡፡
ጉባኤዉ በርካታ ተሞክሮዎች የቀረበቡበት፣ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ኢትዮጵያ አብነት ተደርጋ የተወሰደችበት፣ መሰል ዓለማቀፍ ጉባኤዎችን የማስተናገድ የመሠረተ ልማትና የመስተንግዶ ባህል ዐቅሟና ልምዷ በእጅጉ ማደጉን ያሳየችበት ሆኖም በስኬት ተጠናቅቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት