Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የፋሲል አብያተ መንግስት ጥገና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ ነው – አቶ አረጋ ከበደ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በጎንደር ከተማ የፋሲል አብያተ መንግስት ጥገና ታሪካዊ ይዘቱን ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ ገለጹ።

ርዕሰ መስተዳድሩ በጎንደር ከተማ የሚከናወኑ የልማት ስራዎችን ሂደት ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸው ወቅት እንደገለጹት፤ በጎንደር ከተማ እየተሰሩ ያሉ የልማት ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈፃፀም ላይ ናቸው።

በከተማዋ በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየት ከታየባቸው ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የሆነው የመገጭ ግድብ መስኖ ፕሮጀክት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፍጥነት እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ከሰጡ በኋላ ፕሮጀክቱ ጥራት ጠብቆ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተመሳሳይም የጎንደር አዘዞ መንገድ 12 ኪሎ ሜትር የአስፓልት መንገድ ስራ የኮንትራክተር ለውጥ ተደርጎ በጥሩ ሁኔታ እየተፋጠነ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለፕሮጀክቱ ትኩረት በመሰጠቱ የአፈፃፀም ለውጥ አሳይቷል ብለዋል።

የፋሲል አብያተ መንግስት ጥገና ታሪካዊ ይዘቱን በጠበቀ መንገድ በፍጥነት እየተከናወነ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በአጭር ጊዜ ትርጉም ያለው የቅርስ ጥገና ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።

የከተማዋ የኮርደር ልማት ደረጃውን ጠብቆ እየተሰራ እንደሆነ ጠቅሰው፤ በክልሉ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በጥራት መፈፀም ተችሏል ብለዋል።

የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማጠናቀቅ መንግስት በትኩረት እንደሚሰራ ጠቅሰው፤ በጎንደር ከተማ እየተከናወኑ ያሉ ፕሮጀክቶች አሁን ለደረሱበት አፈፃፀም ዕገዛ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል።

በምናለ አየነው

Exit mobile version