የሀገር ውስጥ ዜና

የሲሚንቶ አምራቾች በመረጧቸው አከፋፋዮች ምርታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ ተገለጸ

By Mikias Ayele

November 08, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሲሚንቶ አምራቾች በመረጧቸው አከፋፋዮች ምርታቸውን ለተጠቃሚው ማቅረብ እንደሚችሉ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

ሚኒስቴሩ ከሲሚንቶ አምራቾች ጋር የምርት አቅርቦትና ፍላጎት ለማጣጣም በሚቻሉባቸው ጉዳዮች ላይ የሚመክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በመድረኩ የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር)÷ የሲሚንቶ ምርት በፍጥነት እያደገ ባለዉ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ዘርፍ ተፈላጊነቱ እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

የሲሚንቶ አቅርቦት አሁን ላይ 7 ሚሊየን ቶን አካባቢ መሆኑን ገልጸው÷ ሀገራዊ የሲሚንቶ ፍላጎትን ለማሟላት ከ20 ሚሊየን ቶን በላይ ምርት ስለሚያስፈልግ በአቅርቦት በኩል ያለዉን ማነቆ በመፍታት የማምረት አቅማቸዉን ወደ 80 በመቶ ከፍ ማድረግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

ከዚህ ቀደም በሚኒስትር መስሪያ ቤቱ በኩል ይደረግ የነበረዉ የሲሚንቶ ግብይት ትስስር መቅረቱን የገለፁት ሚኒስትሩ÷ የሲሚንቶ አምራቾች በመረጧቸው አከፋፋዮች ምርታቸውን ማቅረብ እንደሚችሉ በመግለጽ አቅጣጫ ሰጥተዋል።

መንግስት የሲሚንቶ ገበያዉን ለማረጋጋት በሚያደርገው ቁጥጥር እና ክትትል ላይ ትብብር በማያደርጉ አምራቾች ላይ ግን እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡