አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 29፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና ትግበራን ለማሳለጥ ለዲጂታል አሰራሮች ትኩረት መስጠት እንደሚገባ ተጠቆመ።
በቻይና አውሮፓ ዓለም አቀፍ ቢዝነስ ትምህርት ቤት የአፍሪካ ካምፓስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ማቲው ሳሚኒይ እንዳሉት÷ የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ለሚተገበሩ መርሃ ግብሮች ቴክኖሎጂ ወሳኝ ሚና አለው።
አፍሪካ የንግድና ምጣኔ ሃብት ትስስር በማጠናከር ብልጽግናን እውን ለማድረግ ተግባራዊ ካደረገቻቸው መርሃ ግብሮች መካከል የአፍሪካ አህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣና አንደኛው መሆኑን አስታውሰዋል።
በአህጉሪቱ በሚኖረው 1 ነጥብ 3 ቢሊየን ህዝብ መካከል የሚደረገውን የንግድ ስርአት በማጠናከር አንድነቷ የተጠናከረና የበለጸገች አፍሪካን እውን ለማድረግ ስርዓቱን በቁርጠኝነት መተግበር ተገቢ እንደሆነ ጠቁመዋል።
የኤሌክትሮኒክስ ግብይትን ማስፋፋት፣ የዲጂታል መረጃ አያያዝና ልውውጥን ማጠናከር እንዲሁም በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መተግበር አስፈላጊ እንደሆነ ጨምረዋል።
የቴክኖሎጂ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት፣ የህግ ማዕቀፎችን ማዘጋጀት፣ ትብብርን ማጠናከር እንዲሁም ዘርፉን ለውድድር ክፍት ማድረግ በትኩረት መሰራት ካለባቸው ተግባራት ውስጥ ጠቅሰዋል።
በዚህ ረገድ ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂ መሰረት ልማትን በማስፋፋት፣ ክህሎትን ለማዳበርና ፈጠራን ለማበረታታት እያከናወነች ያለው ተግባር የሚበረታታ እንደሆነ ማንሳታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
በአህጉራዊ ነጻ የንግድ ቀጣናው ሁሉንም ተጠቃሚ ለማድረግ የወጣቶችና ሴቶችን አቅም በዲጂታል ቴክኖሎጂ ለማብቃት ትምህርትና ስልጠና ላይ ትኩረት ማድረግ ተገቢ መሆኑን አስገንዝበዋል።