አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) አምባሳደር እሸቴ ጥላሁን የሹመት ደብዳቤያቸውን ለቤልጂየም ንጉስ ግርማዊ ፊሊፕ አቅርበዋል።
በስነ-ስርዓቱ ንጉስ ፊሊፕ ለአምባሳደሩ ደማቅ አቀባበል ካደረጉ በኋላ ለፕሬዚዳንት አምባሳደር ታዬ አፅቀ ስላሴ የእንኳን ደስ አለዎትና መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡
ግርማዊነታቸው የቤልጂየም እና የኢትዮጵያን የረጅም ጊዜ ግንኙነት በማስታወስ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቱን ማስፋት እና እንደ ማህበራዊ ልማት ባሉ ዘርፎች ትብብርን ማጠናከር ያለውን ጠቀሜታ አመልክተዋል።
በኢትዮጵያ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ፣ የአፍሪካ ቀንድ እና ኢትዮጵያ በአንዳንድ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ላይ ያላትን አቋም ጠይቀው ፥ አምባሳደር እሸቴ የኢትዮጵያን ወቅታዊ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ሁኔታ እንዲሁም ቀጠናዊ ዕድሎችን እና ተግዳሮቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ሰጥተዋል።