የሀገር ውስጥ ዜና

የትምህርት ሚኒስቴር ከሩሲያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር የስምምነት ሰነድ ተፈራረመ

By Shambel Mihret

November 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የትምህርት ሚኒስቴር ከሩሲያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ጋር በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በትብብር ለመስራት የሚያስችለውን የስምምነት ሰነድ ተፈራርሟል።

ስምምነቱ፥ በእኩልነት፣ በጋራ ተጠቃሚነትና ውጤታማነት መርህ ላይ በመመስረት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በጋራ ለመስራት የሚያስችላቸው መሆኑ ተመላክቷል።

በሀገራቱ መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የበለጠ በማጠናከር በትብብር የሚሰሩበትን ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር ያለመ ስምምነት መሆኑም ተገልጿል።

በመግባቢያ ስምምነት ፊርማ ሥነ ስርዓቱ ላይ የተገኙት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ሩሲያ ከኢትዮጵያ ጋር የረጅም ጊዜ ታሪካዊ ግንኙነት እንዳላት አንስተዋል፡፡

በተለይም በአሁኑ ወቅት ሚኒስቴሩ ጥራት ያለው ትምህርት በመስጠት ብቃት ያላቸውና ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆኑ ዜጎችን ለማፍራት በአጠቃላይና ከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በርካታ የሪፎርም ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ለተመራው ልኡካን ቡድን አብራርተዋል።

በኢትዮጵያ የከፍተኛ ትምህርት ዘርፍ የተጀመረው ሪፎርም የበለጠ ውጤታማ እንዲሆንና ከፍተኛ ብቃት ያለው የሰው ሃይል ስለሚፈልግ ሩሲያ ድጋፏን አጠናክራ እንድትቀጥል ጠይቀዋል።

የሩሲያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር በበኩላቸው፥ ስምምነቱ በዓለም አቀፍ ትብብር መሰረት ሁለቱ ሀገራት በከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ በጋራ የሚሰሩበትንና ልምድ የሚለዋወጡበትን ምቹ ሁኔታ የሚፈጥር መሆኑን አንስተዋል።

በዚህም በትምህርት እድል፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት መካከል የልምድ ልውውጥ፣ የመማሪያና ማስተማሪያ ግብዓቶችን መጋራት፣ ሳይንሳዊ ጥናቶችን በጋራ የመስራትና ሌሎች የአቅም ማጎልበቻ ሴሚናሮች በጋራ ለማካሄድ የሚያስችል ስምምነት መሆኑንም ጠቁመዋል።

በመድረኩ የብሪክስ አባል ሀገራት ዩኒቨርሲቲዎች ትብብር፣ ዩኒቨርሲቲዎች በደረጃ የሚቀመጡበት እንዲሁም የድጋፍ ሥርዓት ማዕቀፍ እየተዘጋጀ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) እና የሩሲያ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር የተፈራረሙትን ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት በሁለቱም ሀገራት በኩል የቴክኒካል ቡድን እንደሚቋቋም መገለጹን የትምህርት ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡