የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያና ቼክ ሪፐብሊክ በከባድ ኢንዱስትሪ ማምረቻዎችና በግብርና  በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያዩ

By Mikias Ayele

November 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ እና ቼክ ሪፐብሊክ በከባድ ኢንዱስትሪ ማምረቻዎች፣ በግብርና ፣በመከላከያ እና በሙዚየም ጉዳዮች በትብብር መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ከኢትዮጵያ የቼክ ሪፐብሊክ አምባሳደር  ሚሮስላቭ ኮሼክ ጋር ተወያይተዋል፡፡

በውይይታቸው የረጅም ጊዜ ታሪክ ያለውን የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት ወደ  ተሻለ ደረጃ ማሸጋገር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክክር አድርገዋል፡፡

በተለይም በከባድ ኢንዱስትሪ ማምረቻዎች፣ በግብርና ፣በመከላከያ እና በሙዚየም ጉዳዮች በትብብር መስራት በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

አምባሳደር ምስጋኑ  በዚህ ወቅት ÷የሁለቱ  ሀገራት ግንኙነት የበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  መደበኛ የፖለቲካ ምክክር እና የቢዝነስ ፎረም ማካሄድ እንደሚገባ አንስተዋል።

ኢትዮጵያ እየተገበረችው ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን የገለፁት አምባሳደሩ÷በመሆኑም  የቼክ ሪፐብሊክ ኩባንያዎች በተመረጡ ዘርፎች  እንዲሠማሩ ጠይቀዋል።

አምባሳደር ሚሮስላቭ ኮሼክ በበኩላቸው÷ ሀገራቸው  ከኢትዮጵያ ጋር ያላት ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር  ቁርጠኛ መሆኗን አረጋግጠዋል።

በውይይቱ ሁለቱ ወገኖች በሁለትዮሽ እና በዓለም አቀፍ መድረኮች በትብብር ለመሥራት መስማማታቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመላክታል፡፡