Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

በኮሚሽነር ጄነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑክ ከኢንተርፖል ኃላፊዎች ጋር መከረ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጀነራል ደመላሽ ገ/ሚካኤል የተመራው ልዑክ ከኢንተርፖል ኃላፊዎችና የተለያዩ ሀገራት የፖሊስ ተቋማት ኃላፊዎች ጋር ተወያይቷል፡፡

በእንግሊዝ ስኮትላንድ 92ኛው የኢንተርፖል ጠቅላላ ጉባዔ እየተካሄደ ሲሆን፥ በጉባዔው እየተሳተፈ የሚገኘው የኢትዮጵያ ልዑክ የሁለትዮሽ ውይይቶችን ከተለያዩ ኃላፊዎች ጋር አድርጓል፡፡

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሸነር ጀነራል ከኢንተርፖል ፕሬዚዳንት ሜጀር ጀነራል አህመድ ናስርና በአሁኑ ጉባዔ አዲስ ከተመረጡት ዋና ፀሃፊ ቫልዴዚ ኡርኪዛ ጋር ባደረጉት ውይይት፥ ኢትዮጵያ የድርጅቱን ዓላማ ለማሳካት ቁርጠኛ መሆኗን ገልፀዋል፡፡

በቀጣይ ዓመታት የኢንተርፖል ጠቅላለ ጉባኤን ለማዘጋጀት ኢትዮጵያ ፍላጎት ስላላት የድርጅቱ ፕሬዚዳንትና ዋና ፀሃፊው ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ የጋበዙ ሲሆን፥ ሁለቱም ግብዣውን ተቀብለዋል ተብሏል፡፡

በተመሳሳይ ልዑኩ በእንግሊዝ ከሚገኘውና በኢትዮጵያ የሬድ ፎክሰ ማዕከል ከፍቶ በድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ላይ ከኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ጋር በትብብር እየሰራ ከሚገኘው ናሽናል ክራይም ኤጀንሲ ኃላፊዎች ጋርም ተወያይቷል፡፡

በዚህም በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስና በኤጀንሲው መካከል ስላለው ግንኙነት እንዲሁም የድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል እንዲሁም በቀጠናው ስላሉ የወንጀል ስጋቶች ተወያይቷል።

ልዑካን ቡድኑ እንግሊዝ ለኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየሰጠች ስላለው ሁለንተናዊ ድጋፍ አመስግኗል፡፡

በቀጣይም የተጀመረው የአቅም ግንባታ ድጋፍ እንዲሰፋና በሌሎች ዘርፎችም ትብብርና አጋርነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በጋራ የተዘጋጀው የመግባቢያ ሰነድ በቀጣይ ጥቂት ወራት በአዲስ አበባ ለመፈራረም ተስማምተዋል፡፡

ልዑካን ቡድኑ ከቻይና፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ከናሚቢያ፣ ከኮሎምቢያ፣ ከኳታር፣ ከምስራቅ አፍሪካ ሪጅናል ቢሮ ኃላፊና ከተለያዩ ሀገራት የፖሊስ ኃላፊዎች ጋር በመገናኘት ውይይት አድርጓል፡፡

በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ እየተተገበረ ስላለው ሪፎርም፣ ከአባል ሀገራቱ የፖሊስ ተቋማት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሮ ለማስቀጠልና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎችን በጋራ ለመከላከል የሁለትዮሸ ውይይት አድርጎ ስምምነት ላይ መድረሱን ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

Exit mobile version