ዓለምአቀፋዊ ዜና

የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የጸናባቸው ሀገራት የመከላከያ ክትባት ሊቀበሉ ነው

By Feven Bishaw

November 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ የጸናባቸው ሀገራት የመከላከያ ክትባት ሊቀበሉ መሆኑ ተገለጸ፡፡

በክትባቱ ድልድል ተጠቃሚ የሚሆኑት ሀገራት ማዕከላዊ አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ኮትዲቯር፣ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ኬንያ፣ ላይቤሪያ፣ ናይጄሪያ፣ ሩዋንዳ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ኡጋንዳ ናቸው።

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በአፍሪካ በዚህ ዓመት በበሽታው መያዛቸው ከተረጋገጡ አምስት ሰዎች መካከል አራቱ የሚገኙባት ሀገር ስትሆን ፥ ከተመደበው 900 ሺህ ክትባት 85 በመቶውን ትወስዳለች ተብሏል፡፡

ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ሩዋንዳ ቀደም ሲል የተወሰነ ክትባት መውሰዳቸው ይታወሳል፡፡

በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና በአጎራባች ሀገራት የተከሰተው የዝንጀሮ ፈንጣጣ በዓለም ጤና ድርጅት እና በአፍሪካ ሲዲሲ የህዝብ ጤና ድንገተኛ የአህጉራዊ ደህንነት በነሃሴ ወር የዓለም ስጋት ነው ሲሉ አውጀዋል።

በዚህ ዓመት ብቻ 19 የአፍሪካ ሀገራት የዝንጀሮ ፈንጣጣ በሽታ መከሰቱን ሪፖርት ማድረጋቸው የተገለጸ ሲሆን ፥ አሁንም በሽታው መስፋፋቱን መቀጠሉን ተጠቁሟል።

በሽታው በተስፋፋባት ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በዚህ ዓመት ብቻ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው የተጠረጠሩ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች ደግሞ በበሽታው መሞታቸው ተነግሯል፡፡

የበለጸጉ ሀገራት ለዝንጀሮ ፈንጣጣ ምላሽ የሚሆን ከ3 ነጥብ 6 ሚሊየን በላይ ክትባቶችን ለመስጠት ቃል መግባቸውን የዘገበው አፍሪካ ኒውስ ነው።