Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ምን ይተገብራሉ?

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ በአብላጫ ድምፅ በማሸነፍ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት የሆኑት ዶናልድ ትራምፕ በስልጣን ዘመናቸው ሰባት ዋና ዋና ፖሊሲዎችን ለማስፈፀም ቃል ገብተዋል፡፡

ትራምፕ ወደ ኋይት ሀውስ ሲመለሱ በኢሚግሬሽን፣ በኢኮኖሚ፣ በዩክሬን ጦርነት እና በመካከለኛው ምስራቅ በሚደረገው የእስራኤል-ሃማስ እና ሂዝቦላህ ጦርነት ላይ አዳዲስ ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፉ ይጠበቃል፡፡

ባደረጓቸው የምርጫ ቅስቀሳዎች ላይ ሪፐብሊካን ፓርቲ የሚያሸንፍ ከሆነ ሰባት ዋና ዋና ፖሊሲዎችን ተፈፃሚ እንደሚያደርጉ ለደጋፊዎቻቸው ቃል የገቡ ሲሆን ትናንት ባደረጉት ንግግርም ቃላቸውን እንደሚጠብቁ አረጋግጠዋል፡፡

ትራምፕ ተግባራዊ ለማድረግ ቃል የገቧቸው ሰባት የፖሊሲ አጀንዳዎች ምን ምን ናቸው?

  1. ህጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከሀገር ማስወጣት

ትራምፕ ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ ከሚያስፈጽሟቸው ፖሊሲዎች ቀዳሚው የሰነድ አልባ ስደተኞች ጉዳይ ሲሆን ፕሬዚዳንቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰነድ አልባ ዜጎችን ከአሜሪካ እንደሚያስወጡ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም ህገ ወጥ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ የሚከለክለውን እና በቀድሞ የስልጣን ዘመናቸው የተጀመረውን የሜክሲኮ ድንበር የአጥር ግንባታ ለማጠናቀቅ ይሰራሉ።

  1. ኢኮኖሚ፣ ታክስ እና ታሪፍን በተመለከተ

በፕሬዚዳንት ጆ ባይደን አስተዳደር ዘመን የተከሰተውን የዋጋ ግሽበት ለማረጋጋት ቃል ገብተዋል፡፡ በተጨማሪም የግብር ቅነሳ ለማድረግ ቃል የገቡት ትራምፕ፤ የፍጆታ እቃዎች እና ማህበራዊ ዋስትና ላይ የተጣለውን ግብር እንደሚቀንሱ ይጠበቃል፡፡

  1. አሜሪካ ከዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ስምምነቶች እንድትወጣ ማድረግ

ትራምፕ በመጀመሪው የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው አሜሪካን በመቶዎች ከሚቆጠሩ የአካባቢ ጥበቃ ስምምነቶች እንድትወጣ ያደረጉ ሲሆን ሀገሪቱ ከዓለም አቀፉ የፓሪስ የአየር ንብረት ስምምነት እንድትወጣ አድርገዋል፡፡

ይህን ያደረጉት በዋናነት የአሜሪካን የመኪና ኢንዱስትሪ ለማገዝ ሲሆን በባይደን አስተዳደር የነበረውን የኤሌክትሪክ መኪና ምርት ተነሳሽነት በመተው በነዳጅ የሚሰሩ መኪኖች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በተጨማሪም የከርሰ ምድር ነዳጅ ማምረት ለመጀመር እና ታዳሽ የሀይል ምንጮት ላይ ትኩረት ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡

  1. የዩክሬንን ጦርነት ማስቆም

የዩክሬንን ጦር ለማጠናከር በሚል በአሜሪካ ሴኔት የተደረገውን ከ10 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገንዘብ ሲቃወሙ የቆዩት ትራምፕ፤ ወደ ቢሮ በገቡ በ24 ሰዓት ውስጥ ጦርነቱን በድርድር ለማስቆም ቃል ገብተዋል፡፡

  1. ፅንስ ማቋረጥ ህግን በተመለከተ

ትራምፕ በፈረንጆቹ 2022 በአሜሪካ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የፀደቀውን የፅንስ ማቋረጥ ህግ እንደማይሽሩ የገለፁ ሲሆን፤ የአሜሪካ ግዛቶች የስነ ተዋልዶ ፖሊሲን በተመለከተ የራሳቸውን ህግ ማውጣት እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡

  1. የጥር 6 አማፂያን በሚል ክስ ለእስር የተዳረጉትን በይቅርታ መፍታት

ትራምፕ በ2021 ጥር 6 ቀን ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ቢሯቸውን ለመልቀቅ ፈቃደኛ አለመሆናቸውን ተከትሎ ደጋፊዎቻቸው በፈጠሩት ሁከት በካፒቶል ሂል ህንፃ ፊት ለፊት ግጭቶች ተፈጥረዋል፡፡

በግጭቱ የተጠረጠሩ ከ1 ሺህ 500 በላይ የሪፐብሊካን ደጋፊዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከ1 ሺህ በላይ በሚሆኑት ላይ ውሳኔ ተላልፎባቸውል፡፡ በመሆኑም ወደ ስራ ሲገቡ ለእስረኞቹ ምህረት እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡

  1. በአሜሪካ ፍትህ መስሪያ ቤት መምሪያ ልዩ አማካሪ የሆኑትን ጃክ ስሚዝ ማሰናበት

ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ በሁለት ሴኮንዶች ውስጥ ለማሰናበት ቃል የገቡት በአሜሪካ ፍትህ መምሪያ ልዩ አማካሪ የሆኑትን እና በእርሳቸው ላይ የተካሄዱ ሁለት የወንጀል ምርመራዎችን የመሩትን ጃክ ስሚዝን ነው፡፡

ጃክ ስሚዝ ትራምፕን የ2020 ምርጫን ለመቀልበስ ጥረት አድርገዋል በሚል እንዲሁም ሚስጥራዊ ሰነዶችን ያለአግባብ በመጠቀም በሚል በዶናልድ ትራምፕ ላይ ከስ መመስረታቸው ይታወሳል፡፡

 

47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ሆነው የተመረጡት ዶናልድ ትራምፕ ከአስደናቂው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ድል በኋላ እነዚህን እና ሌሎች ዓለም አቀፋዊ የፖሊሲ ሃሳቦችን ይዘው በመጭው የፈረንጆቹ አዲስ አመት ወደ ኋይት ሀውስ ይመላሳሉ፡፡

Exit mobile version