አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ረሃብ የተባበረ ዓለም ዓቀፍ ምላሽን ይፈልጋል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለፁ፡፡
በአዲስ አበባ እየተካሄደ በሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት መልዕክት÷ የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም የሚችል ግብርናን ማረጋገጥ የዘላቂ የምግብ ዋስትና መሰረት ነው ብለዋል።
የዘላቂ የምግብ ዋስትና ስትራቴጂክ አጋርነትን ይፈልጋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ኢትዮጵያ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ፕሮግራም ቀርጻ እየሰራች እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡
በተለይም ለሴት አርሶ አደሮች የሚደረገው ድጋፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ወሳኝ መሆኑን ገልጸው፤ ረሃብ የተባበረ ዓለም ዓቀፍ ምላሽን ይፈልጋል ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የኢንዱስትሪ ልማት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ገርድ ሙለር÷ ረሃብን ከዓለም ለማጥፋት የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይፈልጋል ብለዋል።
ያደጉ ሀገራትም ከዚህ በፊት ረሃብን ለማጥፋት የገቡትን ቃል ሊጠብቁ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
ገርድ ሙለር በሚቀጥሉት 10 ዓመታት 50 ቢሊየን ዶላር በማፍሰስ በመላው ዓለም ያለውን ረሃብ ማጥፋት እንደሚቻል ገልጸው÷ ይህም ሀገራት ከሚመድቡት ወታደራዊ በጀት ሁለት በመቶው ያህል ነው ሲሉ ጠቁመዋል፡፡
በዚህም የዓለም ሀገራት፣ አጋር አካላት እና ሁሉም ባለድርሻ አካላት ሊረባረቡ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የኬንያው ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ በበኩላቸው÷ በኢትዮጵያ እየተደረገ እንዳለው ረሃብን ለመግታት የሚደረገውን ጥረት በፖሊሲ በመደገፍ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡
በጉባኤው የሴራሊዮን ፕሬዚዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ፣ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ አውሪ ባህ፣ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀ መንበር ሞኒክ ናሳናባንጋዋ ፣የተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና የብራዚሉ ፕሬዚዳንት ሉላ ዳሲልቫ ደግሞ በበይነ መረብ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በምስክር ስናፍቅና አሸናፊ ሽብሩ