የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ ከተመድ የወንጀልና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽ/ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኝነቷን ገለጸች

By Feven Bishaw

November 07, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽ/ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት ገለጸች።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ አዲስ ከተሾሙት የተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል የምሥራቅ አፍሪካ ዳይሬክተር አሺታ ሚታል ጋር ተወያይተዋል።

በውይይታቸው በምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ስጋት የደቀነውን የህገ ወጥ የሰዎች፣ የአደገኛ ዕፅ፣ የሀሰተኛ መድኃኒት እንዲሁም የህገ ወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከላከል በትብብር ለመስራት ተስማምተዋል።

በተጨማሪም የኮንትሮባንድ ንግድ እና በሙስና ከሀገር የሚሸሽ ገንዘብን በመከላከል ረገድ በትብብር ለመስራት ስምምነት ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመልክቷል።

አምባሳደር ምስጋኑ ኢትዮጵያ እነዚህን ጨምሮ ለቀጣናው ስጋት የሚደቅኑ ወንጀሎችን ለመከላከል ከተመድ የወንጀል እና አደገኛ ዕፅ መከላከል ጽ/ቤት ጋር በትብብር ለመስራት ያላትን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።

አሺታ ሚታል በበኩላቸው ከኢትዮጵያ ጋር በትብብር እና በቅንጅት መሥራት በቀጣናው ብሎም በአፍሪካ ችግሩን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ እንደሆነ ተናግረዋል።

ጽ/ቤታቸው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው ተቋማት የሚያደርገውን የአቅም ግንባታ እና የቴክኒክ ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።