አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ እና የተባበሩት ዓረብ ኤሚሬቶች መካከል ያለውን የኢንቨስትመንት እና ንግድ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችል አሠራር ለመመስረት ከስምምነት ተደረሰ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) በተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴዔታ ከሆኑት ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን ጋር ተወያይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በፈታኝ ወቅት ላይ በነበረችበት ጊዜ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች ከጎኗ በመሠለፍ እውነተኛ አጋራነቷን ማስመስከሯን ጌዲዮን (ዶ/ር) በውይይቱ ላይ ገልጸዋል፡፡
የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት እና የሕዝቦችን ወንድማማችነትም ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩ ተናግረዋል።
ሼህ ሻክቡት ቢን ናህያን አል ናህያን በበኩላቸው ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው÷ የሁለትዮሽ ግንኙነቱን ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።
በኢንቨስትመንት እና ንግድ ዘርፎች ያለውን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ማድረስ የሚያስችል አሠራር ለመመስረት በውይይቱ ወቅት ከስምምነት መደረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ አመላክቷል፡፡
በተጨማሪም በአካባቢያዊ ብሎም ቀጣናዊ የሰላም እና ደኀንነት ጉዳዮች ላይ መምከራቸው ነው የተገለጸው፡፡