የሀገር ውስጥ ዜና

ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ናት- ፕሬዚዳንት ታዬ

By ዮሐንስ ደርበው

November 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነቷን ለማረጋገጥ በትክክለኛ ጎዳና ላይ ትገኛለች ሲሉ ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴ ተናገሩ።

በኢትዮጵያ እየተካሄደ የሚገኘው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት እንደነበርም ተናግረዋል።

በጉባዔው ለመሳተፍ ለመጡ ለአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ ሚኒስትሮችና የተቋማት ኃላፊዎች የእራት ግብዣ ተደርጓል።

በመርሐ-ግብሩ ላይም ፕሬዚዳንት ታዬ አፅቀ ሥላሴና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን ጨምሮ የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ፣ የሴራሊዮን ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት ጁሌስ ማዳ ባዮ፣ የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር አማዱ ኡሪ ባህ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬቶች የአፍሪካ ጉዳዮች ሚኒስትር ዴዔታ ሸኸ ሻክቦት ቢንናህያን ተገኝተዋል።

ፕሬዚዳንት ታዬ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ ረሃብ በርካታ የአፍሪካ ሀገራትን የፈተነና ችግር ፈቺ መፍትሔ የሚሻ የጋራ ጉዳይ መሆኑን በአጽንኦት ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያም ረሃብ የሚያስከትለውን ጉዳት በጽኑ ትገነዘባለች ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

አሁን ላይ ኢትዮጵያ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በሚያስችል ትክክለኛ መንገድ ላይ እንደምትገኝም አስታውቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በስንዴ ምርት ራሷን ከመቻል ባለፈ ለውጭ ገበያ መላክ የሚያስችል አቅም መፍጠሯን ጠቅሰው÷ በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እያበረከቱ ያለውን የመሪነት ሚና አድንቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አርሶ አደሮችን በቅርበት ከማገዝ ጀምሮ በግብርናው ዘርፍ ስትራቴጂካዊ ለውጦችን አስመዝግበዋል ሲሉም አብራርተዋል፡፡

በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለው “ከረሃብ ነፃ ዓለም” ጉባዔ በርካታ ጠቃሚ ግብዓቶች የተገኙበት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

በአፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር ምርታማነትና ቀጣይነት ያለው እድገት ለማስመዝገብ መንግሥትና የግሉ ዘርፍ በትብብር መሥራት እንደሚጠበቅባቸውም አስገንዝበዋል፡፡