አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የሥራ ባህልን በማሳደግ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሣደግ በትኩረት እየተሠራ መሆኑን የሥራ፣ ሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ዴዔታ ሰለሞን ሶካ ገለጹ፡፡
በ5ኛው ሀገር አቀፍ ብሔራዊ የሥራ ኤክስፖ በአዲስ አበባ የሚሊኒየም አዳራሽ ተከፍቷል፡፡
ኤክስፖውን ያዘጋጁት የሥራና ክኅሎት ሚኒስቴር ከደረጃ ዶት ኮም እና ከማስተርካርድ ፋውንዴሽን ጋር በመተባበር ነው።
አቶ ሰለሞን በኤክስፖው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር÷ መንግሥት ለዜጎች ጥራት ያለው የሥራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ዛሬ የተከፈተው ኤክስፖም ሥራ ፈላጊዎች እና ቀጣሪ ድርጅቶችን በማገናኘት የሥራ ዕድል ለመፍጠር ያለመ ነው ብለዋል፡፡
ለሁለት ቀናት የሚቆየው ይህ ኤክስፖም ከ30 ሺህ ለሚልቁ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር ያስችላል ነው ያሉት፡፡
የሥራ ባህልን በማሳደግ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ባለፈ ምርትና ምርታማነትን ለማሣደግ እንዲሁም ቤተሰብንና ማኅበረሰብን የምርታማነት ማዕከል ለማድረግ ተቋማቸው በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል፡፡