ዓለምአቀፋዊ ዜና

የሀገራት መሪዎች ለፕሬዚዳንት ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ነው

By Mikias Ayele

November 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የተለያዩ ሀገራት መሪዎች የአሜሪካ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫን ላሸነፉት ዶናልድ ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክታቸውን እያስተላለፉ ይገኛሉ።

ትራምፕ 47ኛው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ለመሆን የሚያስችላቸውን ድምጽ ማግኘታቸውን ተከትሎ የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታኒያሁ የእንኳን ደስ ያለዎት መልካም ምኞት መግለጫ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው÷ ትራምፕ ወደ ኋይት ሀውስ መመለሳቸው የአሜሪካ እና የእስራኤልን ግንኙነት የበለጠ ያጠናክረዋል ብለዋል፡፡

የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ሳሚ አቡ ዙህሪ÷ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ቢሯቸው ሲገቡ በመካከለኛው ምስራቅ የሚደረገውን ጦርነት ለማስቆም ሚናቸውን እንደሚወጡ ያላቸውን ተስፋ ገልፀዋል፡፡

የብሪታኒያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኬር ስታርመር በበኩላቸው፤ በሚቀጥሉት ጊዜያት ከዶናልድ ትራምፕ ጋር በትብብር ለመስራት ጓጉቻለሁ ብለዋል፡፡

አሜሪካ እና ብሪታኒያ በጋራ የልማት ትብብሮች፣ በሰላምና ደህንነት እንዲሁም በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ያላቸው ትብብር የበለጠ እንሚጠናከርም ተናግረዋል፡፡

በተመሳሳይ የህንዱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ÷ ዶናልድ ትራምፕ በማሸነፋቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸው፤ በሁለተኛ ዙር የፕሬዚዳንትነት ዘመናቸው የበለጠ ስኬት እንደሚያስመዘግቡ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

የአሜሪካ እና ህንድ ስትራቴጂክ እና ዓለም አቀፋዊ ትብብርን አጠናክሮ ለማስቀጠል በጋራ እንደሚሰሩም ገልፀዋል፡፡

የሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦርባን÷ ዶናልድ ትራምፕ በመመረጣቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል።

በተመሳሳይ የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑኤል ማክሮን፣ የጀርመኑ ቻንሰለር ኦላፍ ሾልዝ፣ የዩክሬኑፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ፣ የጣሊያኗ ጠቅላይ ሚኒስር ጆርጂያ ሜሎኒ፣ የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስት ፔድሮ ሳንቼዝ እና የአየርላንዷ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳይመን ሃሪስ ለፕሬዚዳንት ትራምፕ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በአንጻሩ ደግሞ ኢራን የዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን መመለሱ የደህንነት ስጋት እንሚፈጥርባት ገልጻለች።

ትራምፕ በኢራን የነዳጅ ምርት ላይ ተጨማሪ ማዕቀብ ሊጥሉ እንደሚችሉ እና እስራኤል የኑክሌር ማበልፀጊያዎቿን እንድትመታ ትዕዛዝ ሊሰጡ እንደሚችሉ ያላትን ስጋት አጋርታለች።