Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ መዋዕለ ነዋያቸውን እንዲያፈሱ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ የተካሄደው የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የፈጠረውን ዕድል በመጠቀም የኦስትሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት አማራጮች ላይ እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ የኦስትሪያ የፌዴራል መራሔ መንግሥት ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ፒተር ላውንስኪ ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ ኢትዮጵያና ኦስትሪያ ረጅም ዘመናትን ያስቆጠረ ግንኙነት እንዳላቸው ያስታወሱት አምባሳደር ምስጋኑ፤ ኢትዮጵያ ከኦስትሪያ ጋር ያላትን የንግድ እና የኢንቨስትመንት ግንኙነት ለማሳደግ ፍላጎት አላት ብለዋል።

የኦስትሪያ ባለሃብቶች እና ኩባንያዎች በኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የተፈጠሩ የኢንቨስትመንት እድሎችን እንዲጠቀሙም ጥሪ አቅርበዋል።

አምባሳደር ፒተር ላውንስኪን በበኩላቸው፤ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አድንቀው፤ ኦስትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ሰፊ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማድረስ ፍላጎት እንዳላት ገልጸዋል።

ሁለቱ ወገኖች በባለብዙ ወገን መድረኮች ያለውን የሁለቱን ሀገራት ትብብር ማሳደግ በሚቻልባቸው መስኮች እና የጋራ ጠቀሜታ ባላቸው ጉዳዮች ዙሪያ መምከራቸውን የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።

Exit mobile version