አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ሐሰተኛ የኦንላይን ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ሲሰጡ በነበሩ 339 ህገ-ወጥ አካውንቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ገለጸ።
ከንግዱ ማኅበረሰብ ጋር በመመሳጠር የንግድ ሥርዓቱ እንዳይቀላጠፍ ሲሰሩ የነበሩ በየደረጃው የሚገኙ 136 ሠራተኞችና አመራሮች ላይም ቢሮው ሕጋዊ እርምጃ መውሰዱ ተገልጿል።
በተያዘው በጀት ዓመት ባለፉት ሦስት ወራት የኦንላይን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥ ላይ የተስተዋሉ ክፍተቶችና የተወሰዱ የመፍትሔ እርምጃዎችን አስመልክቶ የቢሮው ምክትል ኃላፊ ፍስሐ ጥበቡ በሰጡት መግለጫ÷ የንግዱ ዘርፉ ፍትሃዊ፣ ተወዳዳሪና ተደራሽ እንዲሆን ዘመናዊ የአሠራር ሥርዓት ተዘርግቶ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም በ11ዱ ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች የኦንላይን የአሠራር ሥርዓት በመዘርጋት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን ቀልጣፋና ፈጣን ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል።
በዚህ ሂደት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አሰጣጥን የቴክኖሎጂ አሠራር ሥርዓት ለታለመለት ዓላማ እንዳይውል በሰባት ክፍለ ከተሞች 339 የሚሆኑ ህገ-ወጥ አካውንቶች በመክፈት አገልግሎት ሲሰጡ መገኘታቸውን አረጋግጠዋል።
በተከፈተው ሐሰተኛ አካውንት ግብር ሳይከፍሉ የንግድ ፈቃድ እድሳት፣ አዳዲስ የንግድ ፈቃድ፣ ዘርፍ መቀየርና የካፒታል ለውጥ አገልግሎት ሲሰጥ መገኘቱን ተናግረዋል።
በሐሰተኛ የኦንላይን አካውንት አገልግሎት የንግድ ምዝገባና ፈቃድ የተሰጡ 430 አገልግሎቶች ሥራ ላይ እንዳይውሉ ተደርጓም ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ሕብረተሰቡ በተቋሙ ትክክለኛ አካውንት ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንደሚያገኝ አስረድተው፤ በተሳሳተ አካውንት የሚሰሩ ሰዎችንም እንዲያጋልጥ ጠይቀዋል።