የሀገር ውስጥ ዜና

የ4 ክልሎች የጋራ ሃብት የሆኑ የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም ግምገማ እየተካሄደ ነው

By Shambel Mihret

November 06, 2024

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች፣ የደቡብ ኢትዮጵያ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የሲዳማ ክልሎች የጋራ ሃብት የሆኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸምና አጠቃላይ ተቋማቱ ያሉበትን ደረጃ የሚገመግም የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው፡፡

በቀድሞው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል መንግስት ተቋቁመው የነበሩ እና አራቱም ክልሎች ሲደራጁ የጋራ ሃብት ሆነው እንዲቀጥሉ የተወሰኑ የመንግስት የልማት ድርጅቶች አፈጻጸም ነው እየተገመገመ የሚገኘው፡፡

የደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት (ደሬቴድ)፣ የደቡብ ካፒታል አክስዮን ማህበር፣ የኦሞ ባንክ እንዲሁም ሴራዴፍ ኮርፖሬት አፈጻጸም ግምገማ መድረክ የየክልሎቹ ርዕሳነ መስተዳድሮች፣ የልማት ድርጅቶቹ የሥራ ኃላፊዎች እና የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡

በመድረኩ የልማት ድርጅቶቹ በአፈጻጸም ያስመዘገቧቸውን ውጤቶች እና ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በመገምገም እንዲሁም በቀጣይ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች ላይ በመወያየት አቅጣጫ ይቀመጣል መባሉን ደሬቴድ ዘግቧል፡፡