አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ ሕገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና መመረጧን የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ አስታውቋል።
በዚምባብዌ ቪክቶሪያ ፎልስ ከተማ በተካሄደው 7ኛው የአፍሪካ ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤቶችና መሰል ተቋማት ጉባዔ ላይ ነው ኢትዮጵያ የኮሚቴው አባል ሆና የተመረጠችው።
ጉባኤው ”ሰብዓዊ ክብርን መሰረታዊ እሴትና መርሕ ማድረግ፣ የሕገ መንግሥት አተረጓጎም መነሻ እንዲሁም መሰረታዊ የሰብዓዊ መብቶች እና ነፃነቶች ጥበቃና አፈፃፀም” በሚል መሪ ሃሳብ ተካሂዷል፡፡
የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ ወዬሳ፥ ኢትዮጵያ በመድረኩ የነበራት ንቁ ተሳትፎ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሆና እንድትመረጥ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል።
ይህም ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያላትን ተሳትፎና ተደማጭነት ከማሳደግ ባለፈ ሕገ መንግስት ትርጉም ላይ የተሻለ አፈፃፀም ካላቸው ሀገራት ልምድ እንድትቀስም ያስችላታል ብለዋል።
ጉባዔው ሀገራት በሕገ-መንግስታዊ ፍትሕና ዳኝነት ላይ ልምድ የሚለዋወጡበት መሆኑን አንስተዋል፡፡
ይህም የአፍሪካ ሕገ-መንግስታዊ ፍርድ ቤቶች በትብብር እንዲሰሩና ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን እንዲያስከብሩ ዕድል የሚሰጥ ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።