አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 27፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ አምባሳደሮች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሂደትና በደረሰበት ደረጃ መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡
የህዳሴ ግድቡን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ጎብኝተዋል።
ጉብኝቱን አስመልክቶ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር ኢ/ር)፥ በሃይድሮሜት ጉባዔው ኢትዮጵያ በአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ያስመዘገበችውን ስኬት በሳይንሳዊ መንገድ አስደግፈን ያቀረብነውን ጥናት በጉብኝቱ በተግባር ያሳየንበት ነው ብለዋል።
ከዚህ ባለፈም የሕዳሴ ግድብ ውሃ ገድቦ የሚያስቀር ብቻ ሳይሆን ለታችኞቹ የተፋሰስ ሀገራት በቂ ውሃ የሚለቅ መሆኑንም ለአምባሳደሮቹ ማስገንዘብ የተቻለበት እንደነበር ጠቁመዋል።
የዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡም በጉብኝቱ መደነቁን እና ግንዛቤ ማግኘቱን ገልጸው፥ በቀጣይም መሰል ሁነቶች ከመፍጠር ጀምሮ በተለያዩ ቋንቋዎች የኢትዮጵያን እውነት የማሳወቁ ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በጉብኝቱ ከተሳተፉት መካከል በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ በበኩላቸው፥ በግንባታው ሂደት እና ደረጃ መደነቃቸውን ገልጸዋል፡፡
ግድቡ እዚህ ስኬት ላይ እንዲደርስ ያልተቆጠበ ርብርብ ያደረጋችሁ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እንኳን ደስ አላችሁ ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በራስ አቅም የትውልድ ትልቅ አሻራ ማስቀመጥ መቻል ትልቅ ኩራት ነው፤ ኢትዮጵያም ይህን አሳክታለች ያሉት ደግሞ በኢትዮጵያ የሕንድ አምባሳደር አኒል ኩማር ናቸው።
አጠቃላይ ስለግድቡ ገለፃ እንደተደረገላቸው ያነሱት አምባሳደሩ፥ ግድቡ ቀጣናዊ ትብብርን የሚያጠናክር ከመሆኑም በላይ ጠቀሜታው ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለተፋሰሱ ሀገራት ጭምር መሆኑን ተረድቻለሁ ብለዋል።
በወንድሙ አዱኛ