Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ሪፎርሞች በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ሊታገዙ ይገባል – የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ)የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሥራዎች በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች የመረጃ ተደራሽነትን በማጠናከር ለስኬታማነታቸው የበለጠ መስራት እንደሚገባ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡

አገልግሎቱ የመንግስት ዋና ዋና የማክሮ ኢኮኖሚ አፈጻጸም እና የአገልግሎቱ የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምን ገምግሟል፡፡

የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት÷ በኢኮኖሚዉ ዘርፍ እየታየ ያለዉን ለውጥ ለማስቀጠልና የባለድርሻ አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ለማስቻል የሚዲያ እና ኮሙኒኬሸን ሥራ መጠናከር ይኖርበታል፡፡

መንግስት ሀገሪቱ እየተገበረች ያለው የማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ ስራዎች ተግባራዊ ለማድረግ እና ዉጤታማነቱን ለማረጋገጥ በትኩረት ሲሰራበት መቆየቱን ያነሱት ሚኒስትሩ ይህም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጨባጭ ለዉጦችን አሳይቷል ብለዋል፡፡

በሁሉም ዘርፎች የመንግስትን ገቢ ማሳደግ፣ የሀገሪቷ ገቢና ወጪ እንዲመጣጠን ማድረግ፣የልማት ድርጅቶችን ተወዳዳሪነት ማረጋገጥ፣ የመንግስት የመፈጸም አቅም ማሳደግ፣ ተኪ ምርቶችን ማሳደግና ወደ ዉጪ የሚላኩ ምርቶችን መጨመር፣ እንዲሁም ለዜጎች የስራ እድል መፍጠር በማክሮ ኢኮኖሚ መሻሻያ ስራዎች የተመዘገቡ ተጨባጭ ዉጤቶች መሆናቸዉን ለአብነት መጥቀሳቸውን የአገልግሎቱ መረጃ አመላክቷል፡፡

እነዚህን የተመዘገቡ ዉጤቶች በሚዲያና ኮሙኒኬሽን ሥራዎች ተደራሽ ከማድርግና ቀጣይነታቸውን ለማረጋጥ ከመስራት አኳያ ውስንነቶች መኖራቸውን ለገሰ(ዶ/ር) አንስተው÷ በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ የመጣዉን አጠቃላይ ምጣኔ ሀብታዊ እድገት ለማደብዘዝ ከሀገር ዉስጥና ከሀገር ዉጭ የሚቃጡ የሀሰተኛ መረጃዎች ማረም እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

Exit mobile version