Site icon Welcome to Fana Broadcasting Corporate S.C

የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎትና የአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም በጋራ ለመስራት ተስማሙ

 

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ተስማምተዋል፡፡

በአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ የተመራ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባ ገብቷል፡፡

የልዑካን ቡድን አባላቱ ከብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ጋር ረጅም ጊዜ በዘለቀው የትብብር ስራዎች በወቅታዊው ቀጣናዊ፣ አህጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ዙሪያ በስፋት የተወያየ ሲሆን÷ሁለቱ ተቋማት በቴክኒካዊ የመረጃ ዘርፍ እያደረጉት ያለውን የትብብር ማዕቀፍ ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር መስማማታቸው ተገልጿል፡፡

በውይይቱ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ÷ኢትዮጵያ እንደ ሀገር የገጠማትን የፀጥታ ተግዳሮቶች በውይይት ለመፍታት ቅድሚያ ሰጥታ እየሰራች ስለመሆኑና ለቀጣናው መረጋጋት እየሰራች እንደምትገኝ፤ በተጨማሪም በሠላማዊ አማራጮች የባህር በር ተደራሽነት ለማግኘት የጀመረቻቸውን እንቅስቃሴዎች ለልዑኩ አብራርተዋል፡፡

የአልጄሪያ ቴክኒካዊ የመረጃ ተቋም ዳይሬክተር ጀነራል ከሊፋሀ ሚስባሃ በበኩላቸው÷ ተቋማቸው ከአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ጋር የጀመራቸውን የመረጃ ልውውጥ ስራዎችንና የቴክኒካዊ መረጃ የትብብር ማዕቀፎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ልዑኩ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን የጎበኘ ሲሆን በዚህ ወቅት ጀነራል ከሊፋ ሚስባሃ ÷ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብት አቅም አድንቀው ግድቡ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቿም ጭምር የኤሌክትሪክ ኃይል ፍጆታ በማቅረብ እንደሚያገለግልና የትብብር እና አብሮ የመልማት ምዕራፍ የሚከፍት እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በበኩላቸው÷ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ለልዑኩ ያብራሩ ሲሆን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብም ግንባር ቀደሙ መገላጫ መሆኑን እና ከሀገሪቱ አልፎ ለታችኛው ተፋሰስ ሀገራት እንዲሁም ለቀጣናው የሚያበረክተው አዎንታዊ ሚና ከፍተኛ እንደሆነ መናገራቸውን የብሄራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት መረጃ ያመለክታል፡፡

Exit mobile version