አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 26፣ 2017 (ኤፍ ቢ ሲ) የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር) ከአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ከሕብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር በጋራ ጉዳዮች በተለይም በኢትዮጵያ እና አፍሪካ ሕብረት ግንኙነት እንዲሁም በቀጣናዊና አህጉራዊ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ጌዲዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ሕብረት መጠናከር ያላትን ታሪካዊ ሃላፊነት በቁርጠኝነት መወጣቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ሚኒስትሩ ሊቀመንበሩ ለህብረቱ መጠናከር ላደረጉት አስተዋፅኦ ያላቸውን አድናቆትና ምስጋና መግለፃቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል፡፡
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በበኩላቸው ÷ሚኒስትሩ በመሾማቸው የተሰማቸውን ደስታ እንዲሁም በርሳቸው የኃላፊነት ዘመን ሕብረቱ ይበልጥ እንዲጠናከር አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ ተስፋቸውን በመግለጽ መልካም የሥራ ጊዜ እንዲሆንላቸውም ተመኝተውላቸዋል፡፡